የምዕራብ ኦሞ ዞን ገፅታ በከፊል!!!
ምዕራብ ኦሞ ዞን በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ሥር ከሚገኙት ስድስት ዞኖች ውስጥ አንዱ ነው፡፡ ዞኑ በሰባት ወረዳዎች፣ በሦስት የከተማ አስተዳደሮች እና በ115 ቀበሌዎች የተዋቀረ ነዉ፡፡ የምዕራብ ኦሞ ዞን በሰሜን በኩል በቤንች ሸኮ እና ካፋ ዞኖች፤ በደቡብ በኩል በደቡብ ሱዳን፤ በምስራቅ በኩል በደቡብ ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ክልል በደቡብ ኦሞ ዞን፤ በምዕራብ በኩል በጋምቤላ ክልል አኝዋ ዞን ጋር ይዋሰናል።
ዞኑ ከ14ሺህ 584 ስኩዋር ኪሎሜትር ወይም ከአንድ ሚሊዮን 458ሺህ 400 ሄክታር በላይ የቆዳ ስፋት ያለው ሲሆን የስነ ምህዳራዊ ስብጥሩም 57.4% ቆላ፣ 34% ወይና ደጋ፣ እንዲሁም 8.6 % ደጋ ነው፡፡
የዞኑ ህዝብ ብዛት በ1999 በተደረገው የህዝብ እና ቤቶች ቆጠራ መሠረት 345,209 እንደሆነ ይገመታል፡፡ ከ1999 ዓ.ም የህዝብና የቤቶች ቆጣራ በኃላ በሠፈራ ፕሮግራም መጥተው በዞኑ በጎልዲያና በሻሻ አካባቢዎች የሰፈሩ አማራ፣ ሲዳማ እና ከንባታ ህዝቦች በትንቢያው ታሳቢ አልተደረገም፡፡ ከ2000 ዓ.ም ጀምሮ በዞኑ የሠፈሩት የእነዚህ ህዝቦች ቁጥር 95,147 ሲሆን በአሁኑ ወቅት በድምሩ የዞኑ ህዝብ ብዛት 440,356 እንደሆነ ይገመታል፡፡
የምዕራብ ኦሞ ዞን አራት ብሄረሰቦች ከሌሎች የኢትዮጵያ ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ጋር በሠላምና መከባበር የሚኖሩ ሲሆን እነሱም፡-መኤኒት ፣ዲዚ ፣ሱሪ እና ዝልማሞ ናቸዉ፡፡ እነዚህ ብሄረሰቦች የራሳቸው የሆነ ባህል፣ ታርክ፣ ቋንቋ፣ የአለባበስ፣ አኗኗርና አመጋገብ እሴቶች አሏቸው።
በምዕራብ ኦሞ ዞን 532ሺህ 937 ሄክታር መልማት የሚችል መሬት ያለ ሲሆን 169ሺህ 212 ሄክታር መሬት በደን የተሸፈነ ሆኖ ከዚህም ውስጥ የቀርከሃ ደን ይገኝበታል። የዞኑ አመታዊ ሰብል ሽፋን 281ሺህ 894 ሄክታር ሲሆን ከዚህም ውስጥ 101ሺህ 449 ሄክታር መሬት በቋሚ በቋሚ ሰብሎች የተሸፈነ ነው፡፡ 263ሺህ 804 ሄክታር መሬትም በግጦሽ የተሸፈነ ነው፡፡ ዞኑ በቆሎ እና ሌሎች የአገዳ ሰብሎችን በማምረት የሚታወቅ ሲሆን ቅመማቅመምና ቡናም በስፋት ይመረትበታል፡፡ በዞኑ 47 ኢንቨስተሮች ሲኖሩ ከነዚህ ዉስጥ በግብርና ዘርፍ 41 እንዲሁም በኢንዱስትሪ ዘርፍ ስድስት ተሰማርተዋል።
የምዕራብ ኦሞ ዞን በርካታ የተፈጥሮ ሀብት ያለው ሲሆን በተለይ የማዕድን ሀብቱ ተጠቃሽ ነው፡፡ ወርቅና ሌሎች የከበሩ ማዕድናት በስፋት በዞኑ ይገኛሉ፡፡ ዞኑ በእንስሳት ሀብቱም የሚታወቅ ሲሆን የክልሉን ከፍተኛ ቁጥር አርብቶ አደሮችን የያዘ ነው፡፡
ዞኑ በርካታ የቱሪስት መስህቦች ያሉት ሲሆን የኦሞ ብሄራዊ ፓርክ፣ የጨው አፈር፣ ትላልቅ ወንዞችና ፏፏቴዎች፣ ፍል ውሃዎች፣ የሱሪ ብሄረሰብ የዶንጋ ጨዋታ እና ሌሎች አይን ሳቢ የተፈጥሮ ፀጋዎች ባለቤት ነው፡፡ የኦሞ ብሄራዊ ፓርክ ከዞኑ ርዕሰ ከተማ ጀሙ በ184 ኪሎሜትር ርቀት ላይ ይገኛል፡፡ውድንቢ የሚባል እንስሳ በኦሞ ፓርክ ብቻ የሚገኝ ነዉ፡፡ የጨዉ አፈርም ሌላው ቀልብ ሳቢ መስህብ ሲሆን በመኤኒት ሻሻ ወረዳ ዉስጥ የሚገኝ ሆኖ ከዞኑ ርዕሰ ከተማ 60 ኪሎሜትር ይርቃል፡፡
ከመሰረተ ልማት አንጻር ዞኑ ከፍተኛ የተፈጥሮ ሃብት ባለቤት ቢሆንም ከፍተኛ የመንገድ ችግር ያለበት ነው፡፡ በኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣን (ERRA) የሚተዳደር ከዋቻ ማጅ ከተማ እስከ ማጂ ወረዳ ያለው 173 ኪሎሜትር ብቻ ነው፡፡ ከማጂ እስከ ሳይ እየተገነባ ያለው የ33 ኪሎሜትር አስፓልት መንገድ ቢኖርም አገልግሎት ለመስጠት ብዙ ይቀረዋል፡፡ በURP እየተሰራ ካለው 279 ኪሎሜትር መንገድ ውስጥ 180 ኪሎሜትሩ ርክክብ ተደርገው አገልግሎት እየሰጠ ቢሆንም የጥራት ችግር አለበት፡፡
ዞኑ ሁለት የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታሎች፣16 ጤና ጣቢያዎች እና 96 ጤና ኬላዎች አሉት፡፡ የዞኑን የትምህርት ተደራሽነትን ስናይ 11 የአማራጭ ትምህርት ቤቶች፣ 192 የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤቶች፤ 14 የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች በድምሩ 217 ትምህርት ቤቶች እና ሁለት የቴክኒክና ሙያ ኮሌጆች ይገኙበታል፡፡
Nationalities in West-Omo Zone,Me’en, Suri, Diz & Zilmamo

Me’en Nationality

Suri Nationality

Diz Nationality

Zilmamo Nationality










