
በክልሉ ባለፉት አምስት ወራት ከአምስት ቢሊዮን ብር በላይ ካፒታል ላስመዘገቡ ባለሀብቶች የኢንቨስትመንት ፈቃድ ተሰጠ
በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል መንግሥት ከጊዜ ወደ ጊዜ የኢንቨስትመንት ፍሰት እየጨመረ ይገኛል።
በተለይም ክልሉ ከተደራጀ በኋላ በዘርፉ ከፍተኛ ለውጥ ታይቷል። ይህም በአሃዝ ክልሉ ከመደራጀቱ በፊት የኢንቨስትመንት ፍሰት በአመት በአማካይ 25 ከመቶ ከነበረበት አሁን ላይ በአመት ወደ 105 ከፍ ማለት መቻሉም ተመልክቷል።
በዛሬው ቆይታ ከእኛ ጋር እንግዳ! ዝግጅት! የክልሉ የ2018 በጀት ዓመት ያለፉት አምስት ወራት የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴን በሚመለከት የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ንግድና ኢንቨስትመንት ቢሮ ኃላፊ አቶ ታሪኩ አካሉ ከቢሮአችን ጋር ቆይታ አድርገዋል።
”ቆይታ ከእኛ ጋር እንግዳ ዝግጅታችን ”ከቢሮ ኃላፊ ጋር የተደረገው አጠቃላይ ዝግጅት እንደሚከተለው ቀርበዋል፦
መልካም ንባብ!
መንግስት ኮሙዩኒኬሽን ፦ በቅድሚያ ቆይታ ከእኛ ጋር እንግዳ ስለሆኑ እያመሰገንን፤ ስምና ኃላፊነትዎን ቢገልጹልን?
እንግዳችን፦ አመሰግናለሁ! ቆይታ ከእኛ ጋር እንግዳ ስላደረጋችሁኝ! ስሜ አቶ ታሪኩ አካሉ ይባላል የክልሉ ንግድና ኢንቨስትመንት ቢሮ ኃላፊ
መንግስት ኮሙዩኒኬሽን ፦ በክልሉ የኢንቨስትመንት አቅም መለየት፣ያለውን ፖቴንሽያል ከማስተዋወቅም ባሻገር አልሚ ባለሀብቶች በዘርፉ እንዲሰማሩ ምን ሥራዎች እየተሰራ ነው?
አቶ ታራኩ አካሉ፦ ክልሉ ለኢንቨስትመንት አምቅ አቅም አለው ። ያለውን እምቅ አቅም በመለየት ባለሀብቶች በዘርፉ እንዲሰማሩ ፖቴንሽያሉን ማስተዋወቅ ብሎም ወደ አከባቢ የመጋበዝ ሥራ ላይ ልዩ ትኩረት ተሰጥተው እየተሰራ ይገኛል።
በክልሉ ከጊዜ ወደ ጊዜ በኢንቨስትመንት ዘርፍ ለመሰማራት ፍላጎት ያላቸው ባለሀብቶች ቁጥር እየተበራከተ ይገኛል
በዚህም በተለያዩ ዘርፍ ለመሰማራት ፍላጎት ያላቸው ባለሀብቶች ጥያቄዎቻቸውን በመቀበል የተለያዩ አሰራር ሥርዓቶችን በመዘርጋት እየተሰራ በመሆኑ የኢንቨስትመንት ፍሰት ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ መጥቷል።ይህም በክልሉ ከፍተኛ የኢንቨስትመንት ፍላጎት ጥያቄ መኖሩን ያሳያል።
መንግስት ኮሙዩኒኬሽን ፦በክልሉ በ2018 በጀት ባለፉት አምስት ወራት ምን ያህል ካፒታል ላስመዘገቡ ባለሀብቶች የኢንቨስትመንት ፍቃድ ተሰጠ?
አቶ ታሪኩ አካሉ፦ በበጀት ዓመቱ ባለፉት አምስት ወራት ከአምስት ቢሊዮን 271 ሚሊዮን ብር በላይ ካፒታል ላስመዘገቡ ባለሀብቶች የኢንቨስትመንት ፍቃድ ተሰጥቷቿል።
እነዚህም 34 በግብርና፤ 3 በኢንዱስትሪ እንዲሁም አምስቱ በአገልግሎት ዘርፍ በአጠቃላይ ለ42 ባለሃብቶች የኢንቨስትመንት ፍቃድ መስጠት ተችሏል፡፡ በዚህም በበጀት ዓመቱ ባለፉት አምስት ወራት 6 ሺህ 797.13 ሄክታር መሬት ለአልሚ ባለሀብቶች ማስተላለፍ ተችሏል።
መንግስት ኮሙኒኬሽን፦ በኢንቨስትመንት ዘርፍ ለሚሰማሩ ባለሀብቶች ምቹ ሁኔታዎችን ከመፍጠር አኳያ የተከናወኑ ተግባራት ?
አቶ ታሪኩ አካሉ፦በክልሉ በተለያየ ዘርፍ ለሚሰማሩ ባለሃብቶች ምቹ ሁኔታዎችን ከመፍጠር አኳያም በተለይ የመሬት ፖቴንሺያል ለይቶ መሬቱን ወደ መሬት ባንክ ለማስገባት ጥረት እየተደረገ ነው፡፡
አሁን ላይ በየዞኖች ከ70 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት ልየታ የተደረገ ሲሆን በቀጣይ ይህንን መሬት በተገቢው በማስጠናት በዞን እና በክልል ደረጃ ወደ መሬት ባንክ የማስቀመጥ ስራ የሚሰራ ይሆናል፡፡
ይህ ባለሃብቱ ወረዳና ቀበሌ በመውረዳ መሬት ፍለጋ ሚያባክነውን ጊዜና ሃብት የሚያስቀር ይሆናል፡፡ ሌላው አሳሪ የሆኑ ህጎችን በማሻሻል ደንብና መመሪያዎች ወቅታዊ እንዲሆኑ የማድረግ ስራ ተሰርቷል፡፡
ለኢንቨስትመንት ማበረታቻ ከቀረጥ ነጻ ለሚጠይቁ ባለሃብቶች በአካል መጠየቅ ሳያስፈልግ ባሉበት ሆነው ጥያቄያቸውን ለማቅረብ የሚያስችል የኦንላይን ፕላትፎርም ተዘርግቷል፡፡
የኢንቨስትመንት መዳረሻ መንገዶችን በመንግስት ደረጃ ከሚሰራው በተጨማሪ ባለሃብቱን በማስተባበር እየተሰራ ይገኛል፡፡
መንግስት ኮሙዩኒኬሽን ፦ በኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶች የተደረገው የቁጥጥርና ኦዲት ሥራዎች ካለ ቢገለጽ ?
አቶ ታሪኩ አካሉ፦ በክልሉ በተያዘው በጀት ዓመት ባለፉት አምስት ወራት በ10 የግብርና ኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶች ላይ የኦዲት ስራ ተሰርቷል። በዚህም በስድስት ፕሮጀክቶች ላይ 10 ሺህ 72 ሄ/ር መሬት በትርፍ የተያዘውን ተመላሽ እንዲሁም ለ4 ፕሮጀክቶች ማስጠንቀቂያ ተሰጥቷቸዋል ። በቀጣይም የክትትል፣ ኦዲትና እርምጃ የመውሰዱ ሥራ በተጠናከረ ይቀጥላል።
መንግስት ኮሙዩኒኬሽን ፦የኢንቨስትመንት ዘርፍ ለሥራ ዕድል ፈጠራ ያለውን አበርክቶ ቢገልጹልን?
አቶ ታሪኩ አካሉ፦ ኢንቨስትመንት ዘርፍ ለሥራ ዕድል ፈጠራ፤ለቴክኖሎጂ እውቀት ሽግግር፣ ለማህበራዊ አገልግሎት እንዲሁም ለውጭ ምንዛሬ ግኝት የሚኖረው ፋይዳ ከፍተኛ ነዉ።
በዚህም በበጀት ዓመቱ ባለፉት አምስት ወራት ለ435 ሰዎች በቋሚ እንዲሁም በጊዜያዊነት ለ35 ሺህ 5 መቶ ሰዎች የስራ ዕድል መፈጠር ተችሏል።
በፍቅር ከበደ

እየተደረገ የሚገኘዉ እንቅስቃሴ የሚበረታታ እና ክልሉን ወደ ፊት የሚያስፈነጥር ነው!
እንደ ክልላችን ያሉንን ዕምቅ አቅሞችን እና ፀጋዎችን ወደ ባለፀግነት እና ወደ ዕድል ከመቀየሪያ መንገድ አንዱ እና ቀዳሚዉ ኢንቨስትመንት ነው ።