ከእጥፍ በላይ ምርት የሚሰጠው ‘መልካም’ የተሰኘው የማሽላ ዘር ለአርሶ አደሩ ሊቀርብ መሆኑ ተገለጸ

Spread the love

የቦንጋ ግብርና ምርምር ማዕከል፣ የአካባቢውን አርሶ አደሮችና የክልሉን የማሽላ ዘር ፍላጎት ለማሟላት “መልካም” የተሰኘ ምርጥ የማሽላ ዘር እያባዛ መሆኑን አስታወቀ። ማዕከሉ በቤንች ሸኮ ዞን ጉራፈርዳ ወረዳ በሚገኘው የኦትዋ ንዑስ ምርምር ጣቢያ እያካሄደው ባለው የዘር ብዜት፣ በሄክታር እስከ 60 ኩንታል የሚደርስ ምርት የሚሰጠውን ይህን ዝሪያ ለአርሶ አደሩ ተደራሽ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑ ተገልጿል።

የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር አቶ አማኑኤል አለሙ እንደገለጹት፣ በአካባቢው ያሉ አርሶ አደሮች የሚጠቀሙበት ነባር የማሽላ ዝሪያ በሄክታር 23 ኩንታል ብቻ የሚያስገኝ ነው። በአንጻሩ በምርምር የተገኘው “መልካም” የተሰኘው አዲስ ዝሪያ በሄክታር ከ55 እስከ 60 ኩንታል ምርት እንደሚሰጥ በተግባር ተረጋግጧል።

ይህ ዝሪያ ከ15 የማሽላ ዓይነቶች ጋር ተወዳድሮ በምርታማነቱ፣ ቶሎ በመድረሱ እና በሽታን በመቋቋም የተሻለ ሆኖ በመገኘቱ መመረጡን አቶ አማኑኤል አብራርተዋል።

የቦንጋ ግብርና ምርምር ማዕከል ዳይሬክተር አቶ ዘላለም አባቴ በበኩላቸው፣ ማዕከሉ ከመልካሳ ምርምር ማዕከል ያመጣውን ይህን ምርጥ ዘር በ1.5 ሄክታር ማሳ ላይ በማባዛት ላይ እንደሚገኝ ገልጸዋል። ከዚህ ማሳ 120 ኩንታል መነሻ ዘር እንደሚጠበቅና ይህም ለአካባቢው አርሶ አደሮች እንደሚከፋፈል ተናግረዋል።

የተባዛው መነሻ ዘር ለምርጥ ዘር አባዥ ድርጅቶች፣ ለግብርና ሥራዎች ኮርፖሬሽን እና ለተደራጁ አርሶ አደሮች ተደራሽ እንዲሆን በቅንጅት እንደሚሰራ ተጠቁሟል።

የቦንጋ ግብርና ምርምር ማዕከል በሥሩ ባሉ ዞኖች ሌሎች የቴክኖሎጂ ሥራዎችንም እያከናወነ መሆኑን የገለጹት አቶ ዘላለም፣ በካፋ ዞን ሞዲዮ ምርምር ጣቢያም 5 ሄክታር ላይ የዋለው “ቢኤች 661” የተሰኘ የበቆሎ መነሻ ዘር ምርት መሰብሰብ መጀመሩን አክለው ገልጸዋል።

በተከተል ወ/ሚካኤል

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *