በምርጫ ክልል ደረጃ የድምፅ ማዳመር ሥራ እየተከናወነ ነው – ምርጫ ቦርድ

Spread the love

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ሜላትወርቅ ኃይሉ በወቅታዊ የምርጫው ሂደት ዙሪያ በሰጡት መግለጫ፣ በየምርጫ ጣቢያዎች የድምፅ ቆጠራ ተጠናቅቆ ውጤት መለጠፉን እና አሁን ላይ በምርጫ ክልል ደረጃ የማዳመር ሥራ በስፋት እየተከናወነ እንደሚገኝ አስታውቀዋል።

ሰብሳቢዋ በመግለጫቸው እንዳብራሩት፣ በልዩ ልዩ ምክንያቶች ዘግይተው የነበሩ የምርጫ ጣቢያዎችን የድምፅ ቆጠራ ሂደት ትናንት ማጠናቀቅ የተቻለ ሲሆን፣ በአሁኑ ወቅት በሁሉም የምርጫ ጣቢያዎች የተመዘገቡ ውጤቶች ለሕዝብ ዕይታ ክፍት ሆነው ተለጥፈዋል።

ሂደቱን ተከትሎም በምርጫ ክልል ደረጃ የማዳመር ሥራ እየተሠራ እንደሚገኝ እና የምርጫ ክልል ውጤቶችም ወደ ዋናው የምርጫ ማዕከል መምጣት መጀመራቸውን ሰብሳቢዋ ገልጸዋል።

በዚህም መሠረት በውጤት ማመሳከሪያ እና መሙያ ቅጾች ላይ የሰፈሩት መረጃዎች ከየምርጫ ጣቢያው ወደ ምርጫ ክልል እየመጡ መሆኑን ጠቁመዋል።

እነዚህ መረጃዎች ወደ ምርጫ ክልሉ ሲደርሱም በጣቢያዎቹ በአካል ከተሰጠው ድምፅ አንጻር ትክክለኛነታቸው በጥብቅ እየተመሳከረ ርክክብ እየተፈጸመ እንደሚገኝ የቦርዱ ሰብሳቢ አብራርተዋል።

በተጨማሪም የድምፅ ቆጠራ እና ማዳመር ሂደቱን ትክክለኛነት የሚያረጋግጡ የምርጫ ጣቢያ አረጋጋጮች ሥልጠና ከዛሬ ጀምሮ መሰጠት መጀመሩን በመግለጫው ተመላክቷል ሲል ኢቢሲ ዘግቧል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *