የተገኘውን ሰላም በማጽናት የመንግስት ልማት ዕቅዶችን በባለቤትነት መደገፍና ለምርጫው ስኬት መስራት ይገባል፦አቶ ነጋ አበራ

Spread the love

በሸካ ዞን ቴፒ ከተማ በወቅታዊ አካባቢያዊና ሀገራዊ ጉዳዮች ዙሪያ ከተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ጋር የውይይት መድረክ በቴፒ ከተማ ተካሂዷል ።

​በመድረኩ የቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች የተገኙት ክልል ብልፅግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት የፖለቲካና አቅም ግንባታ ዘርፍ ኃላፊና የመንግስት ረዳት ተጠሪ አቶ ነጋ አበራ፤ በቴፒ ከተማና አካባቢው አስተማማኝ ሰላም እንዲሰፍን ሕዝቡና የአካባቢው መንግስት ላበረከተው ከፍተኛ አስተዋፅኦ ምስጋና አቅርበዋል።

አክለውም ብልፅግና ፓርቲ በሀገሪቱ የፖለቲካ፣ በኢኮኖሚና ማኅበራዊ ዘርፎች በርካታ ድሎችን ማስመዝገቡንና ሀገራዊ ለውጡም በተሳካ ሁኔታ እየተመራ መሆኑን ገልጸዋል።

ሰላም ለማንኛውም የልማትና የብልጽግና ጉዞ ዋነኛ መሰረት መሆኑን የጠቀሱት አቶ ነጋ የተገኙት ድሎች ይበልጥ እንዲጎለብቱና ሕዝቡ የልማቱ ተጠቃሚ እንዲሆን ዘላቂ ሰላም ወሳኝ መሆኑን አጽንኦት ሰጥተዋል።

ሰላም ለሁሉም የልማት ሥራዎች የማይናወጥ መሰረት መሆኑን በመግለጽም፣ ሕዝቡ የተገኘውን ሰላም በመጠበቅ የተጀማመሩ የልማት ተግባራት ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት አንስተዋል ።

አያይዘውም መንግስትና ፓርቲው የጀመሯቸውን ትላልቅ የልማት ዕቅዶች በቁርጠኝነትና በባለቤትነት ስሜት እንዲደግፍ ለሕዝቡ ጥሪ ያቀረቡ ሲሆን፤ መጪው ሰባተኛው ሀገራዊ ምርጫ ሰላማዊ፣ ነፃ፣ ፍትሃዊና ዲሞክራሲያዊ በሆነ ሁኔታ እንዲጠናቀቅ በትኩረት እየተሰራ መሆኑንም አስታውቀዋል።

​የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የማህበራዊ ክላስተር አስተባባሪና የክልሉ ትምህርት ቢሮ ኃላፊ አቶ አልማው ዘውዴ በበኩላቸው፤ ከህዝቡ ለሚነሱ የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች መንግስት ደረጃ በደረጃ ለመፍታት እየተሰራ ነው ያሉት።

የአካባቢው ሰላም ዘላቂ እንዲሆን የሁሉም ርብርብ እንደሚያስፈልግ ያሳሰቡት አቶ አልማው፤ ሰላም በነፃ ሳይሆን ዋጋ ተከፍሎበት የመጣ በመሆኑ ይህንን የተገኘውን ሰላም መጠበቅ የሁሉም የጋራ ኃላፊነት ሊሆን ይገባል ብለዋል።

የተጀመሩ የልማት ስራዎች ከዳር እንዲደርሱ ህዝቡ ብልፅግና ፓርቲን እንዲመርጥ የጠየቁት አቶ አልማው፤ መጪው ሰባተኛ ሀገራዊ ምርጫ ሰላማዊ፣ ነፃና ዴሞክራሲያዊ በሆነ መልኩ እንዲጠናቀቅ ህዝቡ ሚናውን እንዲወጣ ጥሪ አቅርበዋል።

​የሸካ ዞን ብልፅግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ኃላፊና የመንግስት ዋና ተጠሪ አቶ አለማየሁ አለሙ በበኩላቸው፤ ብልፅግና ፓርቲ የጀመራቸውን ዘላቂ የልማት ዕቅዶች ዳግም ዕድል አግኝቶ እንዲያስቀጥል የህዝቡ ሚና ከፍተኛ መሆኑን ገልጸዋል።

የነገውን የአገሪቱን ዕጣ ፈንታ ለመወሰን ከቡድንና ከግል ጥቅም ይልቅ ሀገር ይቅደም ለሚለው መርህ ቅድሚያ መስጠትና ሀገርን የሚያስቀድም አቅም ያለው ፓርቲ መደገፍ ያስፈልጋል ሲሉም አሳስበዋል።

​የመድረኩ ተሳታፊዎች በሰጡት አስተያየት፤ የተገኘውን ሰላም በማፅናት የመንግስትን የልማት ዕቅዶች በባለቤትነት ስሜት ለመደገፍ ዝግጁ መሆናቸውን አረጋግጠዋል።

ተሳታፊዎቹ አክለውም መጪው ሀገራዊ ምርጫ ሰላማዊና ዲሞክራሲያዊ እንዲሆን የዜግነት ኃላፊነታቸውን እንደሚወጡ ገልጸዋል ሲል የዞኑ ኮሚዩኒኬሽን ዘግቧል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *