




በዳውሮ ዞን፣ የታርጫ ከተማ አስተዳደር የማዘጋጃ ቤታዊ አገልግሎት አሰጣጥን ቀልጣፋና ጊዜ ቆጣቢ በማድረግ የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ለመፍታት በትኩረት እየተሰራ እንደሚገኝ የጽ/ቤቱ ምክትል ስራ-አስኪያጅ አቶ ታደለ አበራ ገልጸዋል።
በጽ/ቤቱ ስታንዳርዱን ተከትሎ ለተገልጋዮች አገልግሎት የማቅረብ እንዲሁም የባለይዞታዎችን መረጃ አያያዝ የማዘመን ስራ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።
የታርጫ ከተማን ጽዳትና ውበት በመጠበቅ ከተማውን ለነዋሪዎች ምቹ፤ ለአልሚዎች ተመራጭ የኢንቨስትመንት መዳረሻ ለማድረግ መሠረተ ልማት የማሳለጥ ስራ በስፋት እየተከናወነ መሆኑን የገለጹት አቶ ታደለ በከተማ መሬት ልማትና አስተዳደር፣ የይዞታ ምዝገባና ማረጋገጥ እንዲሁም የህብረተሰብ ተሳትፎና ተጠቃሚነት በማሳደግ የማዘጋጃ ቤታዊ አገልግሎት አሰጣጥን የማዘመን ስራ በቅንጅት እየተከናወነ መሆኑን አስረድተዋል።
የታርጫ ከተማ በፈጣን ሁለንተናዊ ዕድገት ላይ እንደሚትገኝ የጠቆሙት አቶ ታደለ የከተማውን ገቢ የመሰብሰብ አቅም በማሳደግ በህብረተሰቡ የሚነሱ የመሠረተ ልማት ጥያቄዎች ደረጃ በደረጃ መፍታት እየተቻለ መሆኑን አብራርተዋል።
በዚህም ለከተማው ተጨማሪ ውበትን የሚሰጥ የ2.6 ኪሎሜትር አስፓልት አካፋያ ግንባታ፣ የውስጥ ለውስጥ መንገድ ጥርጊያና ከፈታ፣ የዲች ግንባታ፣ የመብራትና የውሃ መስመር ዝርጋታና አቅርቦት የማሻሻል ስራ በማከናወን ህብረተሰቡን የልማቱ ተጠቃሚ ማድረግ ተችሏል ብለዋል ኃላፊው።
በበጀት ዓመቱ በከተማው በተከናወኑ የመሠረተ ልማት ዝርጋታዎች ጊዜያዊ የሥራ ዕድል ለወጣቶች የፈጠረ እንደነበረ የገለጹት አቶ ታደለ በአጠቃላይ የመሠረተ ልማት የሟሙላት ተግባር ላይ የከተማው ነዋሪዎችና በአከባቢው በተለያዩ ኢንቨስትመንት ላይ የተሰማሩ አልሚ ባለሀብቶች የላቀ አስተዋጽኦ ማበርከታቸውን ተናግረዋል።
በከተማው ለሥራ ፈላጊ ወጣቶች የሥራ ዕድል ለመፈጠር በማቀድ ከ6.5 ሚሊዮን ብር በላይ በሆነ ገንዘብ አራት የዶሮ ክላስተር ሼድ ግንባታ ተጠናቆ ወደ አገልግሎት መግባቱን ያስረዱት ኃላፊው በዚህም ማህበራት ተደራጅተው በዶሮ ልማት ሥራ መሰማራታቸውን ነው የገለጹት።
በቀጣይም በተለያዩ የከተማው ክፍሎች የሚነሱ የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎችን ለመፍታት ጽ/ቤቱ ከባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት እንደሚሰራ የገለጹት አቶ ታደለ በእስካሁኑ የታየው ጠንካራ የህብረተሰብ ተሳትፎ በዘላቂነት ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጠይቀዋል።
ያነጋገርናቸው የከተማው የህብረተሰብ ክፍሎች በበኩላቸው ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የከተማው ማዘጋጃ ቤት የህብረተሰቡን የልማት ጥያቄዎች ለመፍታት የጀመረው እንቅስቃሴ አበረታች መሆኑን በመግለጽ ተግባሩ ቀጣይነት ኖሮት የህዝብ ተጠቃሚነት በዘላቂነት ማረጋገጥ ይገባል ብለዋል።
አስተያየት ከሰጡት የከተማው ነዋሪዎች መካካል በተላይ በ02 ቀበሌ የአረንጓዴ መንደር ነዋሪ የሆኑት አቶ አዲሱ ወራቦ ከዚህ በፊት በአካባቢያቸው መብራት መስመር ባለመድረሱ ከረዥም እርቀት መብራት በመሳብ በቂ ሀይል ሳያገኙ ላልተገባ ወጪ እንደሚዳረጉ በማስታወስ አሁን ላይ ማዘጋጃ ቤቱ በህብረተሰብ ተሳትፎ የመብራት መስመር ዝርጋታና የትራንስፎርመር ተከላ በማድረጉ ተጠቃሚ መሆናቸውን አስረድተዋል።
በዕድገቱ በዛብህ

በዚሁ ይቀጥሉበት