

የሀገርን የወደፊት እጣ ፋንታና ዘላቂ መረጋጋት ለማረጋገጥ ወጣቶችን በሰላም፣ በአንድነትና በአዎንታዊ ተሳትፎ ዙሪያ ማደራጀት ቀዳሚ ተግባር ሊሆን እንደሚገባ ተጠቆመ።
በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል በሚዛን አማን ከተማ እየተካሄደ በሚገኘው የብሔራዊ የወጣቶች የሰላምና ደህንነት የድርጊት መርሃ ግብር ግብዓት ማሰባሰቢያ መድረክ እየተካሄደ ይገኛል።
የመድረኩ ዋና ዓላማ ወጣቶች በሰላም ግንባታ ሂደት ውስጥ በቂ እውቀት ኖሯቸው በሀገር ግንባታ ላይ የበኩላቸውን አወንታዊ ሚና እንዲወጡና ለብሔራዊ የድርጊት መርሃ ግብሩ የሚሆኑ ጠቃሚ ግብዓቶችን በነፃነት እንዲያንጸባርቁ ማስቻል መሆኑ ተገልጿል።
የመድረኩ መክፈቻ ላይ ንግግር ያደረጉት የቤንች ሸኮ ዞን ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኃላፊና የመንግስት ዋና ተጠሪ አቶ ደግፌ ኩድን የወጣቶች ሰላምና ደህንነት ጉዳይ የአንድ ዘርፍ ወይም የአንድ ተቋም ብቻ ሳይሆን ከሀገሪቱ የወደፊት እጣ ፋንታ ጋር በቀጥታ የተያያዘ መሆኑን አፅንዖት ሰጥተዋል።
ዛሬ ያለን ወጣት ትውልድ የሀገራችን ትልቁ ሀብት ነው ያሉት አቶ ደግፌ ይህ በአካል፣ በእውቀትና በፈጠራ የታነጸ የለውጥ ኃይል በትክክል ካልተመራ ለግጭትና ለመከፋፈል ሊጋለጥ ስለሚችል ወጣቱን በአዎንታዊ ተግባራት ላይ ማሰለፍ እንደሚገባ ገልጸዋል።
በተለይም አሁን ካለው ወቅታዊ ሁኔታ ጋር ተያይዞ ያለ ሰላምና መረጋጋት ጤናማ የዴሞክራሲ ሂደት ሊኖር እንደማይችል የጠቆሙት ዋና ተጠሪው ወጣቶች የግጭት መሣሪያ ከመሆን ወጥተው የሰላም አምባሳደር መሆን እንዳለባቸው አሳስበዋል።
አያይዘውም ወጣቶች ሐሰተኛ መረጃዎችን የመከላከል፣ የጥላቻ ንግግርን የመቃወም፣ የመቻቻል ባህልን የማጠናከርና የሃሳብ ልዩነቶችን በጠላትነት ሳይሆን በዴሞክራሲያዊ ውይይት የመፍታት ኃላፊነታቸውን ሊወጡ እንደሚገባ አደራ ብለዋል።
መንግስትም በበኩሉ በስነ-ልቦና ግንባታ፣ በስራ ዕድል ፈጠራና በወጣቶች ተሳትፎ ማጎልበት ላይ በቁርጠኝነት እየሰራ እንደሚገኝ አስታውቀዋል።
የክልሉ የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ ምክትል ኃላፊና የሴቶች ዘርፍ ኃላፊ ወ/ሮ ራሔል ለዊ በበኩላቸው በሀገርም ሆነ በክልል ደረጃ ከ41 በመቶ በላይ የሚሆነው የህብረተሰብ ክፍል ወጣት መሆኑን ጠቅሰው ይህ የህብረተሰብ ክፍል በሰላም፣ በዴሞክራሲና በተለያዩ ሁነቶች ላይ ግንባር ቀደም ተሳታፊና አስተባባሪ መሆኑን ገልጸዋል።
የክልሉ ወጣቶች በሀገር ግንባታና በሰላም ላይ ያላቸው ሚና ከፍተኛ በመሆኑ አደረጃጀቶቻቸውን ይበልጥ በማጠናከር የሃሳብ ሽረሽር ሊያደርጉና ከሀገር የሚጠበቅባቸውን ሚና እየተወጡ እኩል ተጠቃሚነታቸውን ማረጋገጥ እንዳለባቸው አብራርተዋል።
በመድረኩ ላይ “አዎንታዊ ሰላም ኢትዮጵያ” ከተባለው ሀገር በቀል የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅት እና ከሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ የመጡ ከፍተኛ ባለሙያዎች በሰላም ግንባታ ፅንሰ-ሃሳቦችና በድርጊት መርሃ ግብሩ አስፈላጊነት ዙሪያ ሰነዶችን ያቀረቡ ይገኛል።
የሀገር ሰላም የሚጀምረው በወጣቶች አስተሳሰብ እና በወጣቶች ኃላፊነት ነው በሚል መሪ ሀሳብ እየተመራ የሚገኘው ይህ የምክክርና የግብዓት ማሰባሰቢያ መድረክ ወጣቶች ለተባበረችና ለተረጋጋች ኢትዮጵያ ግንባታ የበኩላቸውን አሻራ የሚያስቀምጡበት ሰፊ መሠረት ይጥላል ተብሎ ይጠበቃል።
በመድረኩ ላይ ከሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር እና “አዎንታዊ ሰላም (Positive Peace) ኢትዮጵያ” ከተባለ ሀገር በቀል የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅት የመጡ ከፍተኛ ባለሙያዎች እንዲሁም የክልሉ 6ቱ ዞኖች የወጣቶች አደረጃጀት አመራሮችና የሲቪክ ማህበራት ወጣቶች ተሳትፈዋል ሲል የዞኑ መንግሥት ኮሙኒኬሽን ዘግቧል።
