ሪፖርታዥ

Spread the love

የክልሉ  ጠቅላይ ፍርድ ቤት የስራ እንቅስቃሴ

ፍርድ ቤት ከሦስቱ የመንግስት አካላት ማለትም የህግ አውጪ፣  ህግ አስፈፃሚ እና ህግ ተርጓሚ  አካል አንዱ ሲሆን በህግ አውጪ የወጣውን ህግን የመተርጎም ተግባር የሚያከናወን፣ ዳኝነት የመስጠት ስልጣን ያለው አካል ነው። ፍርድ ቤት በፈደራልም ሆነ በክልሉ መንግስት የወጡ ወንጀል ህግ፣ የፍትሐብሔር ህግ፣ አስተዳዳራዊ ህግ እና ሌሎችን ህጎችን በሥነ-ሥርዓት ህጎች መሠረት በገለልተኝነት በማከራከር የዳኝነት አገልግሎትን የሚሰጥ ተቋም ነዉ፡፡ የክልሉ ፍርድ ቤቶች በህዝብ አመኔታ ያተረፉ እንድሆኑ የማድረግ ራዕይ ይዘዉ  እየሰሩ ይገኛሉ፡፡

የፍርድ ቤቶች ተልዕኮም ነፃ፣ ገለልተኛ ዳኝነትን በማሳደግ ለዜጎች  ቀልጣፋ ፈጣን  እና ተደራሽነት  ያለው ውጤታማ  ዳኝነት በመስጠት የህግ የበላይነትን የማረጋገጥ ነው።

በዚህ ፅሁፍ ከላይ ያነሳናቸውን ነጥቦችን ተንተርሰን የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል  ጠቅላይ ፍርድ ቤትን የሥራ እንቅስቃሴ  እንቃኛለን፡፡

የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ከህዳር ወር 2014 ዓ/ም ከተደራጀበት በመጀመሪዎቹ የሶስት ወራት ዕቅድ በማዘጋጀት የክልሉ ፍርድ ቤቶችን ያሉበትን አሁናዊ ሁኔታና ችግሮችን ከዉስጥና ከዉጭ በተዉጣጡ ባለሙያዎች ሳይንሳዊ ጥናት በመስጠናት በጥናቱ ግኝትና ምክረ-ሀሳብ መሰረት የሚመራበት ዓመታዊና የ10 ዓመት መሪ ስትራተጅክ ዕቅድ በማዘጋጀት፣ ተቋሙን በሰዉ ኃይል፣ በማተርያልና የአሰራር ሥርዓቶችን በማደራጀት፣ የዳኝነት አገልግሎት የመስጠት ስራ እየሠራ ይገኛል።

ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ከሚሰጣቸው ዋና ዋና  አገልግሎቶች መካከል በቀጥታ ክስ፣ በይግባኝ ሰሚና በሰበር ሰሚ ችሎት የዳኝነት አገልግሎት መስጠት  እንደሚገኙበት የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ጠቅላይ ፍ/ቤት ፕሬዚዳንት አቶ ቆጭቶ ገ/ማሪያም ገልጸዋል።

የክልሉ ጠቅላይ ፍ/ቤት  ዜጎች  ዳኝነትን በቅርበት እንዲያገኙ በማድረግ ወጪንና ጊዜን ከመቆጠብ  አንጻር በዳውሮና ኮንታ ዞኖች  የምድብ ችሎት በመዘርጋት፣ በምዕራብ ኦሞ ዞን በቱም ከተማ፣ በካፋ ዞን ቦንጋ ከተማና በሸካ ዞን ማሻ ከተማ የተዘዋዋሪ ችሎት በመክፈት ተገልጋዩ ማህበረሰብ ባለበት አከባቢ ሆኖ የዳኝነት አገልግሎት እንድያገኝ እየሰራ እንደሚገኝ የጠቆሙት ፕሬዚዳንቱ በተመሳሳይ የከፍተኛ ፍ/ቤቶች እስከ ወረዳ ማዕከል እንዲሁም የወረዳዎችና የከተማ አስተዳደር ፍርድ ቤቶች ደግሞ እስከ ቀበሌ አገልግሎት ማዕከላት በመውረድ ምድብ ችሎትና ተዘዋዋሪ ችሎት በማደራጀት  አገልግሎት በመስጠት ላይ እንደሚገኙ  አንስተዋል።

ፍርድ ቤቶች በአካል ተደራሽነት ባሻገር የወረዳና የቀበሌ ማህበራዊ ፍርድ ቤቶች ሰፋ ያለ የዳኝነት ሥረ-ነገር ሥልጣን በማዉረድ ወደ ዞን ማዕካላት እና ወረዳ ማዕከላት የሚደረጉ ጉዞዎች እንድቀሩ በማድረግ በቀላል ወጪ ዳኝነት እንድያገኙ ተሰርቷል፡፡ ክልሉ ከመደራጀቱ በፍት ከ500 ብር በላይ ግምት ያለዉን ጉዳይ ወደ ወረዳ ማዕከል ይወሰድ የነበርዉን አሁን እስከ 20ሺህ ብር ድረስ ባሉበት ቀበሌ ማህበራዊ ፍርድ ቤት በማቅረብ ዳኝነት ማግኘት እንደምቻል እንዲሁም ከ300ሺህ ብር በላይ ግምት ያለዉን ጉዳይ ወደ ዞን ማዕከል ይወሰድ የነበረዉን አሁን እስከ 3 ሚሊዮን ድረስ ያለዉ ጉዳይ በወረዳ ፍርድ ቤቶች እንድታይ በመደረጉ ማህበረሰቡ በቀላሉና በቅርበት ሆኖ ዳኝነት አገልግሎት እንድያገኝ ምቹ ሁኔታዎች እንድፈጠሩ የማድረግ ሥራ ተሰርቷል፡፡

ከዚህ በተጨማሪ የዳኝነት አገልግሎት በስፋት ተደራሽ     እንዲሆን በማሰብ ህብረተሰቡ በባህሉ መሰረት አለመግባባቶችን በቀላሉ መፍታት እንዲችል የባህል ፍርድ ቤቶች አዋጅ በማስጸደቅ በየአከባቢዉ የባህል ፍርድ ቤቶችን የማደራጀት ሥራ እየተሰራ ይገኛል፡፡

በ2017 ዓ/ም በግማሽ ዓመቱ  የተከናውኑ ተግባራትን በሚመለከት በየደረጃዉ ባሉ ለፍርድ ቤቶች ከሚቀርቡ ጉዳዮች ላይ 97% ዉሳኔ በመስጠት ዕልባት ለመስጠት ታቅዶ በግማሽ ኣመቱ ከቀረበው 27,480 መዝገብ ውስጥ ከ24,600 በላይ መዝገብ ላይ ውሳኔ በመሰጠቱ የግማሽ ዓመት አፈጻጸም 89.5% መሆኑን ፕሬዚዳንቱ  ገልጸዋል።

የግማሽ ዓመቱ የቀረቡ አዲስ መዝገቦችን ከማጠናቀቅ አንጻር የማጥራት አቅምን 100% ለማሳደግ ታቅዶ ክንውን 96.35% መደረሱ ገልጸው የመዝገብ መጨናነቅን በመቀነስ በአንድ ዓመት ጊዜ ዉስጥ መዝገብ ከመጨረስ አንጻር ክልሉ  ሲደራጅ ከ1.17% ከነበረበት ወደ 1% ለማድረስ ታቅዶ በተሰራው ሥራ አሁን ወደ 1.01% ማድረስ ተችሏል ነው ያሉት አቶ ቆጭቶ።

ፍትህን በሁለት ወር ከመስጠት አኳያ አንድ መዝገብ በተከፈተበት በሁለት ወር ጊዜ ውስጥ ፍትህ ማገኘትን 92% ለማድረስ ታቅዶ አሁን ላይ 88.76% መድረሱን የተናገሩት ፕሬዚዳንቱ የሚሻሩ መዝገቦች የመሻር አቅምን ከፍ ለማድረግ በተሰራው ስራ 90% ለማድረስ ታቅዶ 80.08 % ተከናውኗል ብለዋል።

ትኩረት የሚሹ እንደ የሙስና እና ሌሎች የህዝን ጥቅም የሚጎዱ፣ የሴቶችና ህፃናት ጉዳዮችን በአጭር ጊዜ በመፍታት 100% ለማድረስ ታቅዶ 88.8% መድረሱን ያነሱት አቶ ቆጭቶ ወጪ ቆጣቢ የሆኑ እርቅ ተኮር ስራዎችን ለማጠናከር ታስቦ ከቀረቡ ጉዳዮች ፍርድ ቤቶች  እርቅ እንድያልቁ ወደ ሀገር ሽማግሌዎች በመምራታቸዉ 2009 መዝገቦች በእርቅ እንዲያልቁ መደረጉን ገልፀው ማህበራዊ ፍ/ቤቶችንና የባህል ፍርድ ቤቶችን እስከ ታች ድረስ በማቋቋም ማህበረሰቡ ፍትህን በቅርበት እንዲያገኝ እየተሰራ እንደሆነ አክለዋል።

የዳኝነት ነፃነትን ከማስጠበቅና የዳኝነት አገልግሎት ከማሻሻል አኳያ ከሁሉም በቅድሚያ በዘርፉ የሚታዩ ችግሮችን ለመፍታት በዘርፉ ባለሙያዎች ጥናት በማድረግ በግኝት የታዩትን ችግሮች ወደ ዕቅድ በመቀየር እየተሰራ መሆኑን ያብራሩት ፕሬዚዳንቱ ከዚህ በመነሳት በታችኛው መዋቅር የሚታየውን የውሳኔ ነፃነት ችግር፤ በሰው ሀብትና ፋይናንስ አስተዳደር አካባቢ የሚታየውን የነጻነት ማነቆ ለመፍታት ሰፊ የአሰራር እና አደረጃጀት ማስተካከያና የማሻሻል ሥራዎች እንደተሰሩና እየተሰሩም እንደሚገኝ አንስተዋል።

 የአሰራር ሥርዓት ከመዘርጋት አኳያ የፍርድ በቶችን ሥልጣንና ተግባር የሚወስን አዋጅ፣ የዳኞች አስተዳደር አዋጅ፣ የሸርዓ ፍርድ ቤቶች አዋጅ እንዲዘጋጁ እና እንድጸድቁ በማድረግ ወደ ሥራ እንድገባ ተደርጓል፡፡ አዋጆች ማስፈጸምያ ድንብና መመሪያዎችን በሚመለከት የዳኞች ሥነ-ምግባር እና ዲስፒሊን ደንብ፤ የዳኞች ምልመላና መረጣ መመሪያ፣ የዳኞች ሥራ መዘርዝር መመሪያ፣ የችሎት አመራር መመሪያ፣ የጉዳዮች ፍሰት አመራር መመሪያና የዳኞች ዝዉዉር መመሪያ ተዘጋጅተዉ ወደ ሥራ የተገቡና የዳኝነት ነጻነትን ለማስጠበቅ የተደረጉ ጥረቶች መሆኑን ጠቁመዋል፡፡  የሰው ኃይልን ከማደራጀትና ከማሟላት አኳያ እስከ አሁን ከ100 በላይ ዳኞችን በማስሾም  ከዩኒቨርሲቲ የወጡ ወጣት የህግ ባለሙያዎችን በዘርፉ የማቀላቀል ሥራ  በየደረጃዉ ባሉ ፍርድ ቤቶች የሰዉ ኃይል የማሟላት ሥራ  መሰራቱን ገልጸዋል፡፡

 ከዚህ በፊት የሚታዩ ችግሮች እየተቀረፉ እና እየተሻሻሉ መምጣታቸውን የተናገሩት አቶ ቆጭቶ  ችግሮች በዘላቅነት እንዲፈቱ ትኩረት ተሰጥቶ በቀጣይ እንደምሰራም አብራርተዋል።

ፕሬዚዳንቱ አክለውም የተቋሙን ስራ ውጤታማ ለማድረግ የባለድርሻ አካላት ቅንጅት ወሳኝ በመሆኑ የዳኝነት ነጻነትን በማይጋፋ ሁኔታ በጋራ በቅንጅት መሰራት ባለባቸዉ አስተዳደራዊ ጉዳዮች ላይ የመግባቢያ ሰነድ በመፈራረም ቅልጥፍናና ጥራትን በሚያሳድግ መልኩ አፈፃፀምን በጋራ የመገምገምና የታችኛውን መዋቅር በጋራ የመደገፍና ግብረ መልስ የመስጠት ሥራዎች እየተሠሩ መሆናቸውን ገልፀዋል፡፡

የፍርድ ቤቶችን ችግሮችን በጥናትና በምርምር ለመፍታትም ሆነ የአቅም ግንባታ ሥራዎችንና አስፈላጊውን ድጋፎችን ከማግኘት አንጻር ከፍርድ ቤቶች ሥራ ጋር ግንኙነት ካላቸዉ ከፌዴራል ተቋማትሠ፣ ከሚዛን ቴፒ ዩኒቨርሲቲና ከቦንጋ ዩንቨርሲቲ ጋር በቅንጅትና በትብብር እየተሰራ እንደሚገኝ  አቶ ቆጭቶ አንስተዋል።

የተማረ ሰው ኃይልን በማፍራት በተለይ በአርብቶ አደር አካባቢ የሚታየውን የዘርፉ ባለሙያዎችን እጥረት ለመቅረፍ በክልሉ ከሚገኝ ሚዛን-ቴፒ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመቀናጀት ለ90 ተማሪዎች በመደበኛ ፕሮግራም የህግ የመጀመሪያ ዲግሪ የትምህርት ዕድል መሰጠቱን የጠቆሙት ፕሬዚዳንቱ  ቦንጋ እና በሚዛን ቴፒ እና ወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲዎች ጋር በመተባበር የትምህርት ማሻሻያ ከዲፕሎማ ወደ ዲግር በክረምንት መርሃ ግብር ከ80 በላይ ባለሙያዎች ትምህርት በመማር ላይ እንደሆኑ ጠቅሰዋል ።

ወደ ፍርድ ቤቶች የሚቀርቡ መዝገቦች ከጊዜ ወደ ጊዜ እየቀነሱ መምጣታቸዉንና በወንጀልም ሆነ በፍትሐብሔር መዝገቦች ላይ ከ2016 በጀት ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ስነጻጸር በ2017 በጀት ዓመት መቀነሱን ያነሱት አቶ ቆጭቶ የፍትሐብሔር መዝገቦች 2016 በጀት ዓመት ከነበረበት 26002 በ2017 በጀት  ግማሽ ዓመት በተመሣሣይ ጊዜ  17000 በመሆኑ 9002 መዝገቦች መቀነሳቸውን ያነሱ ሲሆን በወንጀል ዘርፍም በ2016 በጀት ዓመት ከነበረበት 11,380 በ2017 በጀት ዓመት በተመሣሣይ ጊዜ 10,486  በመሆኑ 894 መዝገቦች በመቀነስ መቅረቡን አብራርተዋል።

የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ከተደራጀበት ጊዜ ጀምሮ የሥር መዋቅሮችን በማስተባበር በዳኝነት አገልግሎት አሰጣጥ ላይ በርካታ መሻሻሎችን ያመጣ ቢሆንም በቀጣይ በዳኝነት አገልግሎት ጥራት እና በቴክኖሎጂ ተደራሽነት ላይ በትኩረት እንደሚሰራ አንስተዋል፡፡  ይሁን እንጂ በዘርፉ በቂና ክህሎት የተላበሰ የሰው ኃይል ያለመኖር፣ ለፍትህ አካላት በክልሉ የአቅም ግንባታ የማሰልጠኛ ማዕከል ያለመኖር፣ ቀልጣፋ አገልግሎትን ተደራሽ ለማድረግ የቴክኖሎጂ እጥረት፣ ለስራው ተመጣጣኝ ክፍያና ጥቅማጥቅም ባለመኖሩና በውጭ ካለው ገበያ ጋር ባለመመጣጠኑ የዳኞች ፍልሰት  ችግሮች መኖራቸዉን ፕሬዚዳንቱ አብራርተዋል።

በመጨረሻም ፍትህ የአንድ ወገን ስራ ብቻ ባለመሆኑ ማህበረሰቡ በዳኝነት አገልግሎት አሰጣጥ ላይ በሚታዩ ችግሮች ላይ በንቃት እንዲሳተፍና መረጃ እንድሰጥ፣ ሀሰተኛ ክስና ማስረጃ ላይ የሚታዩ ችግሮች ላይ ባለመሳተፍ እዉነትንና ፍትህ በማረጋገጥ ላይ የድርሻቸዉን እንድወጡ የጠየቁትፕሬዚዳንቱ የፍርድ ቤት ዳኞችና ሠራተኞች በመልካም ሥነ-ምግባር በመላበስ በቅንነት ማህበረሰቡን እንዲያገለግሉ የሚመለከታቸዉ ባለድርሻ አካላትም በፍርድ ቤቶች የሚታዩ ችግሮች እንድፈቱ ተገቢዉን ድጋፍ በማድረግ  ኃላፊነታቸውን በተገቢው እንዲወጡ በህዝቡ አመኔታ ያተረፈ ተቋም ግንባታ ላይ የድርሻቸዉን እንድወጡ ጠይቀዋል፡፡

በጌታሁን ግርማ

One thought on “ሪፖርታዥ

  1. የምገርም እና አስፈላጊ ማብራሪያ ነው!

    ተግባሩም ከየት ወደየት እንደደረሰም ገላጭ እና መሬት ላይ ያለዉን ሀቅ የማይቃረን ነው!

    በገለልተኛነቱ ትኩረት ተሰጥቶ ልቀጥልም ይገባል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *