



ድቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ፕላንና ልማት ቢሮ በአንድ ዕቅድ አንድ ሪፖርትና፣ በስነ ህዝብ መሰረታዊ ጉዳዮች ዙሪያ ለክልል ተቋመት የልማት ዕቅድ ዳይሬክቶሬቶችና ለ6ቱ ዞን መምሪያ ሃላፊዎችና ባለሙያዎች ስልጠና ሰጥቷል።
በመድረኩ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የክልሉ ፕላንና ልማት ቢሮ ምክትል ሃላፊና የማክሮ ኢኮኖሚ ዕቅድ ዝግጅት ክትትልና ግብረ መልስ ዘርፍ ሃላፊ አቶ ሰለሞን በቀለ ቢሮው ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ዕድገትን በማስፈን የክልሉ ሕዝብ ከድህነት ተላቆ በሀገርቱ ኢኮኖሚ ላይ የራሱን ድርሻ በማሳረፍ በ2024 ዓ/ም “ኢትዮጵያ አፍሪካዊት የብልፅግና ተምሳሌት” እንድትሆን ሀገራዊ ራዕይ ሰንቆ እየሰራ ይገኛል ብለዋል፡፡
የስታቲስቲክስና መልካዓ-ምድራዊ መረጃ ስርዓት አስተዳደርና ጥራት ቁጥጥር ስራን በማዘመን በክልልና በሁሉም መዋቅሮች መረጃዎች በአይሲቲ ቴክኖሎጂ፣ የጂ.አይ.ኤስና በአይ.ኤም.ኤ.ኤስ ሶፍትዌር እንዲደገፍ ማድረግ የተቀላጠፈ የመረጃ ስርዓትን ለማደራጀትና ዘመናዊ የአጠቃቀም ስርዓትን ለመከተል ያስችላል ያሉት ሃላፊው ከሚመለከታቸዉ አካላት ጋር ተቀናጅቶ በመስራት የህዝብ ቁጥር ምጣኔን ከኢኮኖሚያዊና ከማህበራዊ እንዲሁም ከተፈጥሮአዊ የሥነ-ምህዳር አቅሞች ጋር ማጣጣምና ሚዛናዊ ሁኔታን መፍጠር ይገባልም ብለዋል።
ተቋማትን የማስተባበር እና በዕቅድ መሠረት የመገምገም፣ ግብረ-መልስ የመስጠት፣ ምዘና የማካሄድ፣ የሚፈለጉ ወቅታዊ ዕቅዶችና ሪፖርቶችን በጊዜና በስታንዳደርዱ መሠረት የማድረስ እና መረጃዎን የማደራጀትና የማዘመን ስራ የክልሉ ፕላንና ልማት ቢሮ ኃላፊነትና ተግባር እንደሆነም በመድረኩ ተጠቁሟል።
በመድረኩ ኢኮኖሚየዊና ማህበራዊ የልማት ፖሊሲዎችን ማዕከል ያደረገ ጥራት ያለው የማክሮ ኢኮኖሚ ማዕቀፎችን በመተንተን የአጭር ፥ የመካከለኛና የረጅም ጊዜ ዕቅድ ዝግጅት ትግበራ፥ እና የድጋፍና ክትትል ስርዓት ይዘረጋል የተባለ ሲሆን የካፒታል ፕሮጀክቶች አፈጻጸምና ፍትሃዊነት ላይ ትኩረት ተሰጥቶ እንደሚሰራም ተመላክቷል።
የቢሮው ምክትልና የመረጃና ስነ ህዝብ ልማት ዘርፍ ኃላፊ አቶ ታምራት መኩሪያ በበኩላቸው አንድ እቅድ አንድ ሪፖርትን በተሟላ መልኩ ተግባራዊ በማድረግ ውጤትን መነሻ አድርጎ ተግባራትን ለመለካት የመረጃ አያያዝና ፍሰት ጥራቱን የጠበቀና ተዓማኒ መሆን እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
የመረጃ ጥራትና ተአማንነት ችግሮች ያልተሻገርናቸው ተግዳሮቶቻችን ስለሆኑ መረጃዎችን በማደራጀትና በማዘመን የሚጠየቁ የሶሽዮ-ኢኮኖሚ መረጃዎችን በወቅቱና በጥራት በማድረስ እና የስነ-ህዝብ ጉዳዮችን በእቅዶች አካቶ የመተግበር ጉዳይ ትርጉምና ትኩረት ተሰጥቶ ሊሰራ እንደሚገባ በመድረኩ ተገልጿል።
በክልላዊ ዳታ ቤዝ አስተዳደር ስርዓት ላይ ሰነዱን ያቀረቡት በቢሮው የስታትስቲክስና ጂኦ-ስፔሻል ዳታ ስራዎች አስተዳደርና ጥራት ቁጥጥር ዳይሬክተር አቶ ፋንታሁን ኦቶሮ የመረጃ ጥራት ችግሮች ላይ ቀጣይ ትኩረት ተሰጥቶ ይሰራል ብለዋል።
በመድረኩ በስነ ህዝብ መረጃ አያያዝ አስተዳደር ዙሪያ የቢሮው ስነ ህዝብና ልማት ዳይሬክተር አቶ መንገሻ ኦይደን ሰነድ አቅርበዋል።
በቀረበው የውይይት ስነድ ከተሳታፊዎች ሁሳብ አስተያየት ተነስተው ምላሽ ተሰጥቷል።
በዉቢት ደበበ
