




የኢፌዴሪ ሠላም ሚኒስቴር ከደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል መንግስት ሠላምና ፀጥታ አስተዳደር ቢሮ ጋር በመተባበር ”በግጭት ቅድመ ማስጠንቀቂያና ፈጣን ምላሽ አሰጣጥ”ዙሪያ ለዞንና ወረዳ ባለሙያዎች የአቅም ግንባታ ስልጠና በቦንጋ ከተማ እየሰጠ ይገኛል።
ስልጠናውን ያስጀመሩት የክልሉ ሠላምና ፀጥታ አስተዳደር ቢሮ ምክትልና የፀጥታ ዘርፍ ኃላፊ አቶ ሀብታሙ አለሙ እንደገለጹት፤ክልሉ ከተመሠረተ የአጭር ዕድሜ ያለው ቢሆንም በክልሉ ሁለንተናዊ ሰላምና ፀጥታ በማረጋገጥ ረገድ በርካታ ስራዎች ተሠርቷል ብለዋል።
ክልሉ ከመመሰረቱ በፊት በተለይም በምዕራብ ኦሞ፣ቤንች ሸኮና ሸካ ዞኖች የነበሩ የፀጥታ ስጋቶችን ከሰላም ሚኒስተርና ከተለያዩ ህብረተሰብ ክፍሎች ጋር በመተባበር ሀገር በቀል እውቀቶችና ሌሎች የግጭት መፍቻ መንገዶችን በመጠቀም በተሰሩ ስራዎች አሁን ላይ አንጻራዊ ሰላም ሊሰፊን ችሏል ነው ያሉት።
በክልሉ አዎንታዊ ሰላምና ፀጥታ እንዲመጣ በየደረጃው ያሉ አካላት ላደረጉት አስተዋጾኦ አመስግነው የመጣው አንጻራዊ ሰላም ተጠናክሮ እንዲቀጥል ግጭቶች ሲኖሩ ቀድሞ መረጃ በመስጠት ፈጣን ምላሽ ተሰጥቶ ለተረጋጋ ሰላምና ፀጥታ እንዲኖር ሁሉም የበኩሉን እንዲወጣ ጠይቀዋል።
ስልጠናው ፈጣን የመረጃ አሰባሰብ እና አተናተንን መሠረት በማድረግ የግጭት አዝማሚያዎችን ቀድሞ በመተንተን የጉዳት ሰለባ ከመሆን አስቀድሞ ለመከላከል እንደሚረዳ ያብራሩት አቶ ሀብታሙ አለሙ ሰልጣኞች ከስልጠናው ያገኙትን እውቀት ወደታች በማውረድ ረገድ የበኩላቸውን ሚና መወጣት ይጠበቅባቸዋል ብለዋል።
በሰላም ሚኒስቴር የግጭት ቅድመ ማስጠንቀቂያ እና ፈጣን ምላሽ ኃላፊ አቶ ሺጋዝ ዳኒ በወቅቱ እንዳሉት በክልሉ ያለው አምቅ የተፈጥሮ ሀብት አውጥቶ መጠቀም እንዲቻል በሰላምና ፀጥታ ላይ በትኩረት መስራት ያስፈልጋል ብለዋል።
ሰላም ሚኒስቴር በሀገሪቱ ዘላቂ ሰላምና ፀጥታ እንዲረጋገጥ የተሰጠውን ተልዕኮ እየተወጣ መሆኑን ጠቁመዋል።
ስልጠናው ለሁለት ቀናት የሚቆይ ሲሆን በግጭት ቅድመ ማስጠንቀቂያና ፈጣን ምላሽ አሰጣጥ፣መረጃ አሰባሰብ እና አተነታተን እንዲሁም ዘላቂ መፍተሔ ማበጀት ላይ ዓላማ ያደረገ ነው።
በዚሁ ስልጠና የፌደራልና የክልል የዘርፉ ኃላፊዎችና ባለሙያዎችን ጨምሮ የዞንና ወረዳ ባለሙያዎች እየተሳተፉ ይገኛሉ።
