





በብልጽግና ፓርቲ በሁለተኛ መደበኛ ጉባኤው ባሳለፋቸው ውሳኔዎችና አቅጣጫዎች ዙሪያ ተቀማጭነታቸውን አዲስ አበባ ካደረጉ የዲፕሎማቲክ ማህበረሰብ አባላት ጋር ውይይት እያካሄደ ነው።
በፓርቲው ዋና ጽህፈት ቤት እየተካሄደ ባለው ውይይት ላይ አምባሳደሮችና የዓለም አቀፍ ተቋማት ተወካዮች ተገኝተዋል።
የብልጽግና ፓርቲ የህዝብ እና ዓለም አቀፍ ግንኙት ዘርፍ ኃላፊ ቢቂላ ሁሪሳ (ዶ/ር) እንደገለጹት፥ፓርቲው በ2ኛ ጉባኤው የዜጎችን ተጠቃሚነት ከፍ የሚያደርጉ ውሳኔዎችን አሳልፏል።
የዛሬው ውይይትም በውሳኔዎች እና አቅጫዎች ላይ ለዲፕሎማቲክ ማህበረሰቡና ለዓለም አቀፍ ተቋማት የተደራጀ መረጃ ለመስጠት ያለመ ነው ብለዋል።
በጋራ ለመስራት የሚያስችሉ ቁልፍ አጀንዳዎች ላይ መግባባት ለመፍጠር ውይይቱ ትልቅ ሚና እንዳለውም ጠቁመዋል።
የብልጽግና ፓርቲ ዋና ጽህፈት ቤት የዓለም አቀፍ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ ነብዩ ስሁል፥ የፓርቲው ሁለተኛ ጉባኤ እና ያሳለፋቸው አቅጫዎች ላይ ገለጻ አድርገዋል።
ፓርቲው በሰጠው አመራር በየመስኩ ስኬቶችን ማስመዝገቡን ጠቅሰው፥ ዘላቂ ሰላምን ማረጋገጥ፣የዘርፎች ሪፎርም፣በምግብ ራስን የመቻል እንዲሁም የትላልቅ ፕሮጀክት ግንባታ አፈጻጸምን በአብነት ጠቅሰዋል።
በቀጣይም ጠንካራ ፓርቲ መገንባት፣አንድ የሚያደርጉ አሰባሳቢ ትርክቶችን መፍጠር፣ ዘላቂ የሰላም ግንባታ ስራዎችን ማጠናከር ላይ አቅጣጫ በማስቀመጥ ወደ ስራ መግባቱን ተናግረዋል።
በኢኮኖሚ መስክም እስካሁን የተመዘገቡ ስኬቶችን በማስቀጠል ከዚህ ዓመት ጀምሮ በቀጣይ ተከታታይ ዓመታት 8 ነጥብ 4 በመቶ አማካይ እድገት ግብ መያዙን ጠቅሰዋል ሲል ኢዜአ ዘግቧል።
