



ኢትዮጵያ እና ብራዚል የጋራ ጥቅማቸውን ባማከለ ሁኔታ የሁለትዮሽ እና የባለብዝሃ ወገን ግንኙነታቸውን የበለጠ ለማጎልበት እንደሚሰሩ አስታወቁ።
ኢትዮጵያ እና ብራዚል ሶስተኛ የፖለቲካ ምክክራቸውን በብራዚል መዲና ብራዚሊያ አካሂደዋል።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ምስጋኑ አርጋ እና የብራዚል የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የአፍሪካ እና መካከለኛው ምስራቅ ጉዳዮች ምክትል ሚኒስትር አምባሳደር ካርሎስ ዱዋርቴ ምክክሩን በጋራ መርተውታል።
ሁለቱ ወገኖች የጋራ ጥቅማቸው በሆኑ የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚ እና የማህበራዊ ጉዳዮች ዙሪያ ፍሬያማ ውይይት ማድረጋቸውን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያመለክታል።
ሀገራቱ በንግድ፣ በኢንቨስትመንት፣ በቱሪዝም እና በግብርና መስኮች የጋራ ትብብር በመፍጠር የኢኮኖሚ ዘርፍ ትስስራቸውን ለማጠናከር እንደሚሰሩ ገልጸዋል።
በግብርናው ዘርፍ ያላቸውን ትብብር ይበልጥ ለማጠናከር እንዲሁም ቱሪዝም፣ ህዝብ ለህዝብ ትስስር እና ስፖርት ዘርፎችን ጨምሮ ግንኙነታቸውን የማጎልበት አቅም ያላቸውን ዘርፎች በሙሉ አቅም ለመጠቀም ከስምምነት ላይ ደርሰዋል።
በውይይቱ አምባሳደር ምስጋኑ ለአምባሳደር ካርሎስ በኢትዮጵያ እየተደረጉ ያሉ ሁሉን አቀፍ የፖለቲካ እና የኢኮኖሚ ሪፎርሞችን አስመልክቶ ገለጻ አድርገውላቸዋል።
የብራዚል ባለሀብቶች የማክሮ ኢኮኖሚ ሪፎርሙ የፈጠረውን ሰፊ የኢንቨስትመንት እድሎች ተጠቅመው በፍጥነት እያደገ ባለው የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ መዋዕለ ንዋያቸውን እንዲያፈሱ ጥሪ አቅርበዋል።
በተጨማሪም ሁለቱ ወገኖች በውይይታቸው ሀገራቱ የሚገኙባቸው ቀጣናዎች ያላቸውን ጠቀሜታ አንስተዋል።
ሀገራቱ በብሪክስ እና ሌሎች የባለብዝሃ ወገን አማራጮች ሰላም እና ደህንነት፣ ዘላቂ ልማት፣ የአየር ንብረት ለውጥ፣ የተባበሩት መንግስታ ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት ማሻሻያ እና የዓለም የፋይናንስ ስርዓት ማሻሻያን ጨምሮ በሌሎች የጋራ አጀንዳዎች በትብብር በሚሰሩበት ሁኔታ ላይም መክረዋል።
አራተኛውን የኢትዮጵያ እና የብራዚል የፖለቲካ ምክክር እ.አ.አ በ2026 በአዲስ አበባ ለማድረግም ተስማማተዋል።
ኢትዮጵያ እና ብራዚል ሰባት አስርት ዓመታትን የተሻገረ ታሪካዊ እና ለረጅም ጊዜ የቆየ ወዳጅነት አላቸው።
የብራዚል ፕሬዝዳንት ሊዊስ ኢናሲዮ ሉላ ዳ ሲልቫ እ.አ.አ በ2024 በኢትዮጵያ ያደረጉት ጉብኝት የሀገራቱን በሁለትዮሽ፣ በብሪክስ ማዕቀፍ እና በሌሎች የባለብዝሃ ወገን የትብብር ማዕቀፎች ያላቸው አጋርነት ላይ ተጨማሪ አቅም መፍጠሩን ሚኒስቴሩ አመልክቷል ሲል ኢዜአ ዘግቧል።
