ክልሉ ከተመሠረተ ወዲህ የንጹህ መጠጥ ውሃ ችግራቸው እየተቀረፈ መሆኑን ነዋሪዎች ተናገሩ

Spread the love

የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ከተመሠረተ ወዲህ ዘመናትን ያስቆጠረ የንጹህ መጠጥ ውሃ ችግራቸው መቀረፉን የዳውሮ ዞን ዛባ ጋዞ ወረዳ ደቼ ደነባ እና የካፋ ዞን ጠሎ ወረዳ ኦሚያ ቀበሌ ነዋሪዎች ተናግረዋል።

ክልሉ ከተደራጀ ወዲህ በዳዉሮ ዞን ዛባ ጋዞ ወረዳ ደቼ ደነባ ቀበሌ በ12 ሚሊዮን ብር ወጪ 2ሺህ 364 የቀበሌ ነዋሪዎችን እና የእንስሳት ውሃ ማጠጫ ገንዳዎችን ያካተተ እንዲሁም በካፋ ዞን ጠሎ ወረዳ ኦሚያ ቀበሌ በ12.7 ሚሊዮን ብር ወጪ 3ሺህ 162 የቀበሌ ነዋሪዎችን ተጠቃሚ ያደረገ የንጹህ መጠጥ ውሃ ሥራዎች ተሰርተዋል።

ያነጋገርናቸው የዳውሮ ዞን ዛባ ጋዞ ወረዳ የደቼ ደነባ ቀበሌ ነዋሪዎች ከዚህ ቀደም በአከባቢያቸው የንጹህ መጠጥ ውሃ አቅርቦት ባለመኖሩ ውሃን ለማግኘት ረዥም መንገድ በመጓዝ እንደሚንገላቱና ህብረተሰቡም ሆነ እንስሳቱ ለዉሃ ወለድ በሽታ ተጋላጭ እንደሚሆኑ ገልጸዋል።

አሁን ክልሉ ከተመሠረተ በአጭር ዓመት ውስጥ የረዥም ዘመናት የህዝቡ የንጹህ መጠጥ ውሃ ጥያቄ በመመለሱ ደስተኛ እንደሆኑና መንግስትም ላደረገላቸው በጎ ምላሽም ነዋሪዎች አመስግነዋል።

ነዋሪዎቹ በአከባቢያቸው የተሰራው የንጹህ መጠጥ ውሃ ፕሮጀክት ለረዥም ጊዜ አገልግሎት እንዲሰጥ የመጠበቅና የመንከባከብ ኃላፈነት እንደሚወጡ በንግግራቸው አረጋግጠዋል።

የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ከመጣ ወዲህ በንጹሕ መጠጥ ውሃ ዘርፍ የሚታዩና የሚጨበጡ ሥራዎች እንደተሰሩም የገለጹት የዛባ ጋዞ ወረዳ የውሃ፣ ማዕድንና ኢነርጂ ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ታምራት አራሮ የደቼ ደነባ ቀበሌ የንጹህ መጠጥ ውሃ አገልግሎት የዚሁ ትሩፋት ውጤት ነው።

በዛባ ጋዞ ወረዳ ደቼ ደነባ ቀበሌ ከዚህ በፊት ምንም የንጹህ መጠጥ ውሃ ሽፋን የሌለው አካባቢዉ ዝናብ አጠርና ተደጋጋሚ ድርቅ የሚከሰትበት በመሆኑ መንግስት የህዝቡን ችግር ከግምት ውስጥ በማስገባት በ2016 ዓ.ም የካቲት ወር ሥራውን በማስጀመር በያዘው በአራት ወራት ውስጥ በማጠናቀቅ ለአገልግሎት አብቅቷል ብለዋል።

በደቼ ደነባ ቀበሌ በ12 ሚሊዮን ብር ወጪ 12 ቦኖዎችና ታንከር እንዲሁም የእንሰሳት ውሃ ማጠጫዎችን ያካተተ ስራ መሰራቱን ጠቁመው በዚህም 2ሺህ 364 የቀበሌ ነዋሪዎችን ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉንም የጽ/ቤቱ ኃላፊው አስረድተዋል።

ባለፉት ረጅም ጊዜያት በዛባ ጋዞ ወረዳ በተለይም ደቼ ደነባ ቀበሌ በንጹህ መጠጥ ውሃ ችግር የሚታወቅ አከባቢ እንደሆነም የዛባ ጋዞ ወረዳ የብልጽግና ፓርቲ ንዑስ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ዳዊት ዳና ገልጸዋል።

ብልጽግና ሰዉ ተኮር ቃልን በተግባር የሚፈጽም ፓርቲ በመሆኑ የደቼ ደነባ የንጹህ መጠጥ ውሃ የህዝብ ጥያቄ ለመመለስ በገባው ቃል መሠረት በማከናወን የህዝቡን የዘመናት ጥያቄ ባጠረ ጊዜ ውስጥ በመመለስ ችግራቸውን ማቃለል በመቻሉ በአከባቢው ህዝብ ሥም ምስጋና አቅርበዋል።

ክልሉ በቀድሞ ደቡብ ክልል ተጀምረው የቆሙ የንጹህ መጠጥ ውሃ ፕሮጀክት ግንባታዎችን በማጠናቀቅ ህዝቡን ተጠቃሚ ከማድረግ ባለፈ የመንገድ መሠረተ ልማት ጥያቄዎቻቸው እንደተመለሱም የገለጹት ደግሞ የካፋ ዞን ጠሎ ወረዳ የኦሚያ ቀበሌ ነዋሪዎች ናቸው።

ነዋሪዎቹም ከዚህም በፊት በኦሚያ ቀበሌ የንጹህ መጠጥ ውሃ እጥረት በመኖሩ ውሃን ፍለጋ ከአንድ ሰዓት በላይ መንገድ ተጉዘው በጀርባቸው ተሸክመው አምጥተው የሚጠቀሙ ሲሆኑ ይህ ችግራቸውም አሁን ላይ መቀረፉንም አንስተዋል።

ክልል ሆኖ ለመደራጀት ገፊ ምክንያት ከሆኑት ጉዳዮች መካከል ህዝቡ በቅርበት አገልግሎት ማግኘትና መንግስትም የህዝቡን ጥያቄ ምላሽ መስጠት እንደሆነም ያነሱት የካፋ ዞን ጠሎ ወረዳ ዋና አስተዳደሪ አቶ አትርሴ ሻታቸው ከግቡ አንጻርም ክልሉ ከመጣ ወዲህ የተሰሩ ሥራዎች አመርቂ ናቸው ብለዋል።

በዚህም በጠሎ ወረዳ ጋባላ ከተማ ትልቅ ጀኔሬተር ተተክለው እና ሪዛይቨር ተዘጋጅቶ ከከተማው ማህበረሰብ አልፎ ጤና ጣቢያዎችና ትምህርት ቤቶችን የንጹሕ መጠጥ ውሃ ተጠቃሚ ማድረጉን ዋና አስተዳዳሪው ጠቅሰዋል።

እንዲሁም በጠሎ ወረዳ ኦሚያ ቀበሌ ናሊ ከተማ የተገነባው የንጹህ መጠጥ ውሃ ለከተማው ህዝብ ከሚሰጠው ጥቅም ባሻገር ኢንቨስት ሊያደርግ የሚችል አካል ቢገኝ እንኳን ሊበቃ የሚችል ትልቅ አቅም ያለው ፕሮጀክት መሰራቱንም አቶ አትርሴ አክለዋል።

በፍቅር ከበደ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *