




የኮይሻ ኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ግድብ ፕሮጀክት የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች እና የደቡብ ኢትዮጵያ ክልሎች አዋሳኝ አካባቢዎች ሕዝቦችን ማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች በሚፈታ መልኩ እየተገነባ መሆኑ ተገለጸ፡፡
በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግሥት ዋና ተጠሪ ሚኒስትር ተስፋዬ በልጅጌ (ዶ/ር) እና ሌሎች ከፍተኛ የመንግሥ ሥራ ኃላፊዎች የኮይሻ ኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ግድብ ፕሮጀክትን ጎብኝተዋል፡፡
በዚሁ ወቅት የፕሮጀክቱ ግንባታ 65 በመቶ መድረሱ የተገለጸ ሲሆን፤ ፕሮጀክቱን በተያዘለት ጊዜ ለማጠናቀቅ ርብርብ እየተደረገ መሆኑም ተጠቅሷል፡፡
በ2 ነጥብ 5 ቢሊየን ዩሮ ወጪ እየተገነባ የሚገኘው ይህ ፕሮጀክት፤ በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል በኮንታ ዞን ኮንታ ኮይሻ ወረዳ እና በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ጎፋ ዞን መሎ ኮዛ ወረዳ መካከል ላይ ይገኛል።
ፕሮጀክቱ የሁለት ክልሎች ሕዝቦችን ማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ችግሮችን በሚፈታ መልኩ እየተገነባ እንደሚገኝም ነው የተገለጸው፡፡
በተጨማሪም የአካባቢው ተፈጥሮ በይበልጥ ተጠብቆ የሚለማበትና ለጎብኚ መስኅብ ከፍተኛ አስተዋጽዖ እንደሚያበረክት መገለጹን ከጎፋ ዞን ኮሙኒኬሽን መምሪያ የተገኘ መረጃ ያመለክታል ሲል ኢዜአ ዘግቧል፡፡
