ከ6 ሺህ በላይ ነዋሪዎችን ተጠቃሚ የሚያደርግ የጸሐይ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክት ተመረቀ

Spread the love

በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል በምዕራብ ኦሞ ዞን ሜኤኒት ሻሻ ወረዳ የተገነባው እና ከ6 ሺህ በላይ ነዋሪዎችን ተጠቃሚ የሚያደርገው የይርኒ የጸሐይ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክት በዛሬው እለት ተመርቋል።

በምረቃ ሥነ ስርዓቱ ላይ ንግግር ያደረጉት በውሃ እና ኢነርጂ ሚኒስቴር የኢነርጂ ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ዶ/ር ኢ/ር ሱልጣን ወሊ፤ ኢነርጂ ለማንኛውም አይነት የልማት እንቅስቃሴ ዋነኛው ግብዓት በመሆኑ ከፍተኛ ትኩረት ተሰጥቶበት እየተሠራ መሆኑን ገልጸው፤ የይርኒ የጸሐይ ኃይል ማመንጫ መገንባቱ ለወጣቶች የሥራ ዕድል ከመፍጠር አንጻር ቀላል የማይባል ሚና ያለው መሆኑን አንስተዋል።

በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት የሥራ አስፈጻሚ ተወካይ እና የኮሙኒኬሽን ሥራ አስፈጻሚ አቶ መላኩ ታዬ በበኩላቸው፤ ለዜጎች አስተማማኝ የኤሌክትሪክ ኃይል ለማድረስ የመልሶ ግንባታ እና ማሻሻያ ሥራዎችን በመሥራት እንዲሁም ተጠቃሚ ያልሆኑ ዜጎችን ደግሞ ፍትሀዊ በሆነ መልኩ ተጠቃሚ ለማድረግ እየተሠራ መሆኑን ገልጸዋል።

ለዚህም ከዋናው የኤሌክትሪክ መረብ ርቀው የሚገኙ የገጠር ከተሞች እና መንደሮችን የጸሐይ ኃይል ማመንጫ በመገንባት ተጠቃሚ ለማድረግ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሠራ መሆኑን ገልጸው፤ በዚህም የይርኒ የጸሐይ ማመንጫ በመገንባቱ ከ 6 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ለአካባቢው ነዋሪዎች እንዲሁም የጤና እና የትምህርት ተቋማት 24 ሰአት የኤሌክትሪክ አገልግሎት ተጠቃሚ ተደርገዋል ማለታቸውን ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡

የይርኒ ጸሐይ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክት ከአፍሪካ ልማት ባንክ በተገኘ ከ 60 ሚሊየን ብር በላይ የገንዘብ ብድር የተገነባ ሲሆን ነዋሪዎቹን ተጠቃሚ ለማድረግ 0.5 ኪሎ ሜትር የመካከለኛ እና 2.4 ኪሎ ሜትር የዝቅተኛ መስመር ዝርጋታ እንዲሁም ባለ 100 እና 200 ኬ.ቪ.ኤ ትራንስፎርመሮች ተከላ ተከናውኗል፡፡

#ደሬቴድ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *