



የሚዛን አማን ከተማ ነዋሪ የሆኑት አቶ ሲራጅ ከተማ በሰጡት አስተያየት በከተማዉ የተጀማመሩ የመንገድ መሰረተ ልማት እና የከተማ ኮሪደር ልማት እንቅስቃሴዎች የከተማዉን ገጽታ የቀየሩ ናቸዉ ብለዋል፡፡
አቶ አዲሱ አለማሁ እና ታምራት ሳንት በበኩላቸዉ የከተማ አስተዳደሩ ህብረተሰቡ ለሚያነሳቸው የልማት ጥያቄዎች ደረጃ በደረጃ ምላሽ እየሰጠ እንደሚገኝ ጠቅሰዉ በከተማዉ እየተከናወነ ያለዉ የኮሪደር ልማት እና በከተማዉ የአገልግሎት ሰጪ ሆቴሎች መሻሻል እንዳስደሰታቸዉ ተናግረዋል፡፡
በከተማ አስተዳደሩ የመሰረተ ልማት ስራዎችን ለማስፋፋት በሚደረገዉ ተስፋ ሰጪ የልማት ተግባራት የሚጠበቅባቸዉን ድጋፍ ለማድረግ ዝግጁ መሆናቸዉን ገልጸዋል፡፡
በከተማዉ አንዳንድ አካባቢዎች የሚስተዋሉ የዉሃና የመብራት አገልግሎት ችግሮችን መፍታት እንደሚገባም አስተያየት ሰጪዎቹ ጠይቀዋል፡፡
የሚዛን አማን ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ኢንጂነር ሰለሞን ሌዊ እንደተናገሩት፤የከተማዉን ደረጃ በማሳደግ ለነዋሪዉ ምቹ ለማድረግ በትኩረት እየተሰራ ይገኛል ብለዋል፡፡
በከተማዉ በህብረተሰቡ ተሳትፎ የተጀመረዉ የኮሪደር ልማት ስራ የከተማዉን ዉበት ከመጨመር ባለፈ የትራፊክ አደጋን ለመቀነስ እና መጨናነቅን ለማስቀረት ያስቻለ ስኬታማ ተግባር እንደሆነም ተናግረዋል፡፡
በከተማዉ ያለፕላን የተዘረጉ መሰረተ ልማቶችን ለማስተካከል በተደረገዉ ጥረት በተገልጋዩ ማህበረሰብ ላይ መጉላላት ሳይፈጠር ቶሎ በማስተካከል አገልግሎቱን በማስቀጠል የልማት ስራዉን ከግብ ለማድረስ መቻሉን ተናግረዋል፡፡
በከተማዉ አንድንድ አካባቢዎች ከመብራት አገልግሎት ጋር ተያይዞ የሚፈጠሩ ችግሮችን ለመቅረፍ እና ከተማዉን የዉሃ ተደራሽነት ለማረጋገጥ ከባለድርሻ አካላት ጋር እየተሰራ እንደሚገኝም አስረድተዋል፡፡
በካሳሁን አሰፋ
