





ከኢፌዴሪ ግብርና ሚኒስቴር እና ከደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ግብርና ቢሮ የተወጣጣ ቡድን በክልሉ በዘላቂ የመሬት አያያዝ ፕሮግራም እየተከናወኑ የሚገኙ ተግባራት ላይ የመስክ ምልከታ አድርገዋል።
ቡድኑ፥ በዳዉሮ ዞን በኢሠራ ወረዳ በጉዛ፣በጉይቲ እና ከጉድሙ ቀበሌዎች በዘላቂ መሬት አያያዝ ፕሮግራም የተሠሩ የአፈና ውሃ ጥበቃ፣ የስነ-አካላዊና ስነ-ህይወታዊ ስራዎች እንዲሁም በፕሮግራሙ የኑሮ ማሻሻያ ማዕቀፍ እየተከናወኑ ያሉ ተግባራትን ተዘዋውረው ጎብኝቷል።
በዘላቂ የመሬት አያያዝ ፕሮግራም በክልሉ አበረታች ተግባራት እየተከናወነ እንደሚገኝ ነው በኢፌዴሪ ግብርና ሚኒስቴር የዘላቂ መሬት አያያዝ ፕሮጀክት ከፍተኛ ባለሙያ አቶ ቦጋለ ገናናው የገለጹት።
እንደ አቶ ቦጋለ ገለጻ፥ በኢትዮጵያ ያለውን ከፍተኛ የመሬት መራቆት ችግር በዘላቂነት ለመቅረፍ መንግሥት ከልማት አጋሮች ጋር በመሆን በርካታ ተግባራትን እያከናወነ እንደሚገኝና በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል እየተከናወነ ያለው ተግባር የዚሁ አካል መሆኑ ነው ያመለከቱት።
የዘላቂ መሬት አያያዝ ፕሮግራም በክልሉ በስድስት ወረዳዎች ተግባራዊ መኾኑን ያመለከቱት አቶ ገናናው በተላይም በዳውሮ ዞን ኢሰራ ወረዳ፣በጨበራ ጩርጩራ ብሄራዊ ፓርክ አቅራቢያ የሚገኙ የህብረተሰብ ክፍሎችን በመደገፍ የፓርኩን ተጽዕኖ ለመቀነስ የጎላ ፋይዳ እንዳለው ተናግረዋል።
በወረዳው ከአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራ በተጓዳኝ በኑሮ ማሻሻያ መርሀ-ግብር የእንሰት ችግኝ ተደራሽ በማድረግ እንደሀገር የተጀመረውን ከተረጂነት ወደ ምርታማነት ለተሟላ ሀገራዊ ሉዓላዊነት ጉዞ ለማረጋገጥ የተጀመረው ተግባር አመርቂ መሆኑን ነው አቶ ቦጋለ የገለጹት።
በ6ሺህ ሄክታር መሬት ላይ የአፈርና ውሃ ጥበቃ ተግባር መከናወኑን የገለጹት የወረዳው ግብርና ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ በቀለ አስፋው ዘርፍ ብዙ ጠቀሜታ ያላቸው የተለያዩ ችግኞችን በመትከል ለአርሶአደሮች ተደራሽ ማድረግ መቻሉንም አብራርተዋል።
በንዑስ ተፋሰስ የተደራጁ ማህበራት በገቢ ማስገኛ ስራዎች ዘርፍም ተሰማርተው ውጤታማ መሆናቸውን የገለጹት ኃላፊው በዚህም በዶሮ፣ በበግና ፍየል እርባታ አርሶአደሮች በስፋት ተሰማርተው እየሰሩ እንደሚገኙ ተናግረዋል።
የፕሮግራሙ አስተባባሪ አቶ ዘላለም አለማየሁ በበኩላቸው ፕሮግራሙ በወረዳው ባለፋት ሶስት ዓመታት በርካታ ተግባራትን መፈጸሙን በመገለጽ ፤ የአከባቢውን አርሶአደሮች የስራ ባህል በማሻሻል በጠንካራ የስራ ባህል ማዳበሩን አስረድተዋል።
በወረዳው 16ሺህ 800 ሄክታር መሬት የሚሸፍን 10 ንዑስ ተፋሰስ መኖሩን ያመለከቱት አስተባባሪው በበጀት ዓመቱ ማጠቃለያ ከእነዚህ ውስጥ የ6ቱን የስነ-አካላዊ ስራ ለማጠናቀቅ በልዩ ትኩረት እየተሰራ እንደሚገኝ አስታውቀዋል።
የቡድኑ አባላት በወረዳው በፕሮግራሙ እየለሙ የሚገኙ የእንሰት እና የአቦካዶ ዝርያ ማሻሻያ፣ የቡና እና የሌሎች ዘርፍ ብዙ ጠቀሜታ ያላቸው ችግኞችን እንዲሁም የእርከን ስራዎችን ተዘዋውሮ ጎብኝተዋል።
በዕድገቱ በዛብህ
