




የደምኢህክመ ገቢዎች ቢሮ የበጀት ዓመቱን ገቢ አሟጦ ለመሰብሰብ የሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ የምክክር መድረክ እያካሄደ ነው።
ቢሮው የ2017 በጀት ዓመት የ10 ወራት የገቢ አሰባሰብና ቀጣይ የትኩረት አቅጣጫ ላይ ያተኮረ የምክክር መድረክ በሚዛን አማን ከተማ እያደረገ ይገኛል።
የቢሮው ኃላፊ ወ/ሮ ህይወት አሰግድ በምክክር መድረኩ ላይ ባስተላለፉት መልዕክት የታክስ ገቢ መንግስት የህዝቡን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ፍላጎት ደረጃ በደረጃ ምላሽ ለመስጠትና ለሚነድፋቸው የልማት ፕሮግራሞችና ፕሮጀክቶች ዋነኛ የፋይናንስ ምንጭ ነው ብለዋል።
በደንበኞች አገልግሎትና በታክስ አወሳሰን የስራ ክፍል እና በገቢ አሰባሰብ ትልልፍና ዕዳ ክትትል ዙሪያ የሚስተዋሉ ችግሮችን ፈጥኖ በመናበብ በየደረጃው ቀርፎ በቀሪ ጊዜያት ገቢን አሟጦ ለመሰብሰብ በትኩረት መስራት ይገባል ብለው በቀጣይ ዓመት አቅደን ለምንፈፅመው ተግባር ግብዓት የሚወሰድበት መድረክ ነው ሲሉ ኃላፊዋ ተናግረዋል።
ወ/ሮ ህይወት አሰግድ አክለውም በቀሪ ሁለት ወራት የሚሰሩ ተግባራት ላይ ከ10 ወራቱ አፈፃፀም ግብዓት በመውሰድ ዕቅዱን ለማሳካት በጊዜ የለኝም መንፈስ ሌት ከቀን የምንሰራት ወቅት ነው ብለዋል።
አቶ ወንዱ ታደሰ የቢሮው ምክትል ኃላፊና የታክስ ኦፕሬሽን ዘርፍ ኃላፊ በበኩላቸው የምክክር መድረኩ ባለፋት ሶስት ዓመታት በገቢ ተቋም የዕቅድ ትግበራ ወቅት የታዩ ክፍተቶችን በዝርዝር ለይቶ በማረም የበጀት ዓመቱን ዕቅድ በስኬት በማጠናቀቅ በቀጣይ የዕቅድ ትግበራ ጊዜያት በቂ ዝግጅት ለማድረግ ይቻል ዘንድ ግብዓት የሚወስድበት መድረክ ስለሆነ የተለየ ትኩረት በመስጠት መስራት እንደሚገባ ተናግረዋል።
አቶ ተመስኬን ተሾመ በገቢዎች ቢሮ የደ በደንበኞች አገልግሎት በታክስ አወሳሰንና የስራ ክፍል በዕቅድ ትግበራ ወቅት የተስተዋሉና መሻገር የሚገባቸው ጉዳዮች ላይ ያተኮረ ሰነድ በዝርዝር አቅርበዋል።
በሰነዱም በግብር ከፋዮች የደረጃ ሽግግር ያለውን ክፍተት በማረም አፈፃፀሙን ማሻሻል እንደሚገባ፣ ለግብር ከፋዮች የሚሰጡ አገልግሎቶች ቀልጣፋና ጥራት እንዲሆን ማስቻል እንደሚገባ፣ የግብር ከፋዮች መረጃ በአግባቡ በማደራጀት ለመረጃ ጠያቂዎች በወቅቱና በጥራት እንዲተላለፍ ማድረግ እንደሚገባ፣ ፍትሃዊና ወቅታዊ የግብር/ታክስ ውሳኔ እንዲወሰን መስራት፣ በግብር ከፋዮ የሚቀርቡ አመታዊ፣ ወርሃዊና የሩብ ዓመት ሪፖርቶች ዴስክ ኦዲት ማድረግ፣ የግብር/ታክስ ውሳኔዎች በቴክኖሎጂ እንዲከወን በቁርጠኝነት መስራት እንደሚገባ አቶ ተመስጌን ተሾመ አብራርተዋል።
ወ/ሮ አዲስዓለም ወልዴ በቢሮው የገቢ አሰባሰብ ክትትል ሂሳብ ማጠቃለያ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር የገቢ አሰባሰብ ትልልፍና ዕዳ ክትትል ዙሪያ የሚስተዋሉ ችግሮች ላይ ያተኮረ ሰነድ አቅርበዋል።
ዳይሬክተሯ ባቀረቡት ሰነድ የተዛባና ያልተሟላ የግብር ከፋይ አድራሻ ምዝገባ፣ የሰራተኛ የስራ ገቢ ግብርን በሲግታክስ አሰባሰብ ዝቅተኛ መሆን፣ ሁለት በመቶ ቅድመ ግብርና በገዥ ተይዞ የሚከፈል 7.5 በመቶ የተጨማሪ አሴት ታክስ ዊዝሆሊዲግ በወቅቱ አለማድረስ ችግር ለዕቅድ ስኬቱ ተግዳሮት በመሆኑ በቀረፍ እንደሚገባው አብራርተዋል።
ለሁለት ቀናት በሚቆየው የምክክር መድረክ የቢሮው ኃላፊዎችና ፈፃሚዎች እንዲሁም የስድስቱ ዞን የገቢ ተቋም አመራሮችና ዳይሬክተሮችና ቡድን መሪዎች መሳተፋቸውን ከቢሮው ያገኘነው መረጃ ያያመለክታል።
