አሜሪካ እና ቻይና የንግድ ውጥረታቸውን ለማርገብ በለንደን እየመከሩ ነው

Spread the love

የአሜሪካ እና የቻይና ከፍተኛ ባለስልጣናት በሁለቱ ልዕለ-ኃያላን ሀገራት መካከል የተፈጠረውን የንግድ ውጥረት ለማርገብ ዛሬ በእንግሊዝ ለንደን ለውይይት ተቀምጠዋል።

በዋሽንግተን እና በቤጂንግ መካከል ያለውን የንግድ ውጥረት ለማርገብ ባለፈው ወር በስዊዘርላንድ፣ ጄኔቫ ከተማ ሁለቱም ወገኖች አብዛኛውን ታሪፍ እንዲያነሱ ያስቻለ ቅድመ-ስምምነት ላይ ደርሰው ነበር።

ዶናልድ ትራምፕ በአገራት ላይ ሊጥሉት ያቀዱትን ታሪፍ ለ90 ቀናት እንዲዘገይ ካሳወቁ በኋላ በአንጻሩ በቻይና ምርቶች ላይ የሚጥሉትን ታሪፍ ደግሞ ወደ 145 በመቶ ከፍ አድርገው ነበር።

በቅድመ ስምምነቱ መሰረት ደግሞ አሜሪካ በቻይና ላይ የጣለችውን ታሪፍ ከ145 በመቶ ወደ 30 በመቶ ዝቅ ለማድረግ እንዲሁም ቻይና በአሜሪካ ላይ የጣለችውን የ125 በመቶ ታሪፍ ወደ 10 በመቶ ዝቅ ለማድረግ ሀገራቱ ውጥን ይዘዋል።

በኋላ ግን ዶናልድ ትራምፕ በማህበራዊ የትስስር ገጻቸው ላይ ቻይና የንግድ ስምምነቱን ሙሉ በሙሉ እንደጣሰች መግለጻቸው ውጥረቱ እንዲያገረሽ አድርጎት ነበር።

ባለፈው ሳምንት ደግሞ በአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ እና በቻይናው መሪ ሺ ጂንፒንግ መካከል ከቀናት በፊት የንግድ ውጥረቱን ለማርገብ ያለመ እና ከአንድ ሰዓት በላይ የፈጀ የስልክ ልውውጥ መደረጉ ይታወሳል።

የዛሬው ውይይትም ሁለቱ ወገኖች በጄኔቫ የተደረሱበትን ቅድመ-ስምምነት ወደ መስመሩ ለማስገባት እንደሚረዳቸው የዋይት ሃውስ ቃል አቀባይ ካሮላይን ሌቪት ለፎክስ ኒውስ ተናግረዋል።

የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ በድጋሚ ወደስልጣን ከመጡ በኋላ በሁለቱ ሀገራት መካከል አንዱ በአንዱ ላይ ከሚጥሉት ቀረጥና አጸፋዊ የታሪፍ እርምጃዎች ባሻገር ከፍተኛ የኤክስፖርት ቁጥጥር እያደረጉ መሆኑን የሮይተርስ ዘገባ ያመላክታል።

ፒተርሰን ኢንስቲትዩት ፎር ኢንተርናሽናል ኢኮኖሚክስ የተባለው የጥናት ተቋም እንዳስታወቀው፤ እ.አ.አ. በ2024 አሜሪካ 143.5 ቢሊዮን ዶላር የሚያወጡ የተለያዩ ምርቶችን ወደ ቻይና ልካለች፤ በአንጻሩ ቻይና 438.9 ቢሊዮን ዶላር የሚያወጡ ምርቶችን ወደአሜሪካ ልካለች ሲል ኢቢሲ ዘግቧል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *