ሪፖርታዥ

Spread the love



የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ከተሞች ፕላን ኢንስቲትዩት የክልሉን ከተሞች ፕላን የማዘጋጀት፣ የከተሞችን ፕላን ትግበራ ሁኔታ የመከታተል እና የክልሉን ክትመት ለማሳደግ የሚያግዙ ተግባራት የመፈጸም ኃላፊነት ተሰጥቶት የተደራጀ ተቋም ነው።


ከተሞች የተቀናጀና አሳታፊ የልማት ዕቅድ ኖሯቸዉ ስርዓት ባለው መንገድ ለምተዉ ከአካባቢያቸው ገጠር እና ከተሞች ጋር ተሳስረው ፈጣን ልማት እንዲያመጡ፣ የከተሞችን ጥያቄ ፍላጎት መሠረት በማድረግ ከተሞችን ማደራጀት፣ ደረጃውን የጠበቀ ፕላን ማዘጋጀት፣መተግበር እንዲሁም መረጃዎች ተደራሽ እንዲሆን ማበረታታት የኢንስቲትዩቱ ዋነኛ ተልዕኮ ነው።
በክልሉ አከታተምን ሥርዓት ባለዉ መልክ ከመምራት አንጻር ልማታቸው በፕላን እንዲመራ፣ ሰፋፊ ከተሞች በዙሪያቸው የሚገኙ አነስተኛ ከተሞችና የገጠር ልማት ማዕከላትን አማክለው በመያዝ ማደግ እንዲችሉ ከደረጃቸው ጋር የሚመጥኑ የተለያዩ የፕላን አይነቶችን በማዘጋጀት እና ትግበራቸውን በመከታተል እንዲሁም በመደገፍ የወጡ የከተማ ፖለሲ እና ስትራቴጂዎችን በመተግበር በክልላችን ምቹ የመስሪያና የመኖሪያ ዘመናዊ ከተሞች ባለቤት እንዲሆን ማድረግ ዓላማውም ነዉ።
የከተማ ፕላን የአንድን ከተማ እና የአካባቢውን የወደፊት ዕድገት የህዝብን ጥቅም መሰረት አድርጎ እንዲመራ የሚዘጋጅ የመሬት አጠቃቀም ዕቅድ ነው፡፡ ያለውን ውስን የከተማ መሬት ሀብት ውጤታማ በሆነ አግባቡ ለመጠቀም እንዲሁም ወሰን የሌለውን የሰው ፍላጎት በቅደም ተከተል ለማሟላት፣ ወደፊት ሊያጋጥሙ የሚችሉ የሰዎች ፍላጎቶች ላይ የተመሰረቱ ግጭቶችን ለመፍታት ከተሞችን በፕላን መምራት አስፈላጊነቱ የጎላ ነው፡፡
የክልሉ የከተሞች ፕላን ኢንስቲትዩት የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልላዊ መንግስት ከተመሠረተ ጀምሮ ከፈርጅ አንድ እስከ ፈርጅ አምስት ለሚገኙ 130 ከተሞች የተለያየ ደረጃ እና ዓይነት ያላቸው የከተማ ፕላኖች ማዘጋጀታቸውን የኢንስቲትዩቱ ዳይሬክተር አቶ ፀጋዬ ኃይሌ ገልጸዋል።
በዚህም 97 የነበረውን የከተሞች ቁጥር ወደ 112 ማድረስ መቻሉን እና የከተማ አስተዳደር ቁጥር ከነበረበት 7 ወደ 20 እንዲደርስ ተደርጓልም ያሉት አቶ ፀጋዬ በ2017 በጀት ዓመት የክልሉ ከተሞች ፕላን ኢንስቲትዩት የተለያዩ ደረጃ እና ዓይነት ያላቸው 44 የከተሞች ፕላን ማዘጋጀቱንም ተናግረዋል።
በፕላን ጥናትና ምርምር ዘርፍ በዳውሮ እና ሸካ ዞኖች ሁለት ስትራክቸራል ፕላን ለማዘጋጀት ታቅዶ በዳውሮ ዞን ቶጫ ከተማ ፕላን በማዘጋጀት የህዝብ ውይይት ተደርጎ ፕላን የማጽደቅ ሥራ ቀርቷል ነው ያሉት ዳይሬክተሩ በ2017 በጀት ዓመት በሸካ ዞን ቴፒ ከተማ ስትራክቸራል ፕላን የከተማ ነባራዊ ሁኔታ ጥናት ተካሂዶ ለባለድርሻ አካላት ቀርቦ አስተያየት ተሰጥቶበት በበጀት አመቱ ለማጠናቀቅ ፕሮፖዛል እየተሰራ እንዳለም ነው የጠቆሙት።
የሠፈር ልማት ፕላን(NDP) መዋቅራዊ ፕላን ተግባራዊ ለማድረግ በአንድ የከተማ ከፍል ላይ የሚዘጋጅ የፕላን አይነት ነዉ። የሚዘጋጀውም መዋቅራዊ ፕላን ተግባራዊ ለማድረግ ሲባል አቅምንና በወቅቱ ያለውን ሁኔታ አገናዝቦ ለመተግበር እንዲቻል ነው፡፡ በዚህም መሰረት በ2017 በጀት ዓመት 4 የሰፈር ልማት ፕላን (NDP) ለማዘጋጀት ታቅዶ በቤንች ሸኮ ዞን ሁለትና በካፋ ዞን 2 ማጠናቀቅ ተችሏልም ብለዋል።
መሰረታዊ ፕላን የሕዝብ ቁጥራቸው ከ2ሺህ እስከ 20ሺህ ለሆነ የፈርጅ 4 እና 5 አነስተኛ ከተሞች የሚዘጋጅ የኘላን አይነት ነው፡፡ በበጀት አመቱ ለ12 ከተሞች ለማዘጋጀት ታቅዶ ቤንች ሸኮ ዞን ለሚገኙ 4 ከተሞች፣ ሸካ ዞን ለሚገኙ 2 ከተሞች፣ በምዕራብ ኦሞ ዞን ለሚገኙ 2 ከተሞች፣ በካፋ ዞን 1 ከተማ እንዲሁም በኮንታ ዞን ለሚገኝ 1 ከተማ በድምሩ በክልሉ ለሚገኙ 10 ከተሞች ለማዘጋጀት እንደተቻለምአቶ ፀጋዬ አብራርተዋል፡፡
የገጠር ማዕከላት የሚኖረው ህዝብ በአብዛኛው ኑሮው በግብርና ላይ የተመሰረተ መሆኑን ያብራሩት ዳይሬክተሩ ይሁንና ካለው ሥርዓተ ከተማ (Urban System) ጋር በተገናዘበ መልኩ ወደ ከተማነት ሲያድጉ ዘርዘር ያለ የመሬት አጠቃቀም የሚያሳይ መሠረታዊ ኘላን እስከሚዘጋጅላቸው ድረስ ዕድገታቸውን በስርዓት ለመምራት የሚያስችል ስኬች ኘላን ይዘጋጅላቸዋል ብለዋል፡፡
ከዚህም መነሻ በተያዘው አመት 15 የስኬች ፕላኖች ለማዘጋጀት ታቅዶ በምዕራብ ኦሞ ዞን 6፣ ቤንች ሸኮ ዞን 4፣ ካፋ ዞን 2፣ ዳውሮ ዞን 2፣ ኮንታ ዞን 1 በድምሩ ለ15 የገጠር አገልግሎት ማዕከላት መዘጋጀቱን ገልጸዋል፡፡
በየከተሞቹ ደረጃ ከሚወጣላቸው ቦታዎች መገኘት ያለበትን ገቢ በመሰብሰብ ከተሞችን ዘመናዊ ለማድረግ የሚደረገውን እንቅስቃሴ ለመደገፍ የሚያስችል አቅም ለመፍጠር፣ ከከተማ ቦታዎች በየደረጃው መገኘት የሚገባውን ገቢ በመሰብሰብ ለከተማው ነዋሪዎች ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና መሰረተልማት አገልግሎቶችን በስፋትና በጥራት ለማቅረብ የሚደረገውን ጥረት ለማሳካት፣ ከተሞች የቦታ ደረጃ ጥናት ይካሄድላቸዋል ብለዋል አቶ ፀጋዬ፡፡
በመሆኑም በዚህ የበጀት አመት ለ12 ከተሞች ለማዘጋጀት ታቅዶ በካፋ ዞን 6፣ ቤንች ሸኮ ዞን 3፣ ሸካ ዞን 3 በድምሩ ለ12 ከተሞች ለማዘጋጀት መቻሉን የገለጹት ዳይሬክተሩ የፕላን ትግበራ ውስን የሆነውን የከተማ መሬት ሀብት በአግባቡ መጠቀምና ተያያዥ በርካታ የፋይናንስ፣ ቁሳዊ ሰብአዊ ሀብቶቸን በማስተዳደር ለዜጎች ተገቢ አገልገሎት የመስጠት ጉዳይ እንደሆነ አስረድተዋል፡፡
የከተሞች ፕላን ትግበራ ስራ የተዘጋጁ ፕላኖች ወደ መሬት ለማውረድ የሚያስችሉ ተግባራትን እንዲሁም የትግበራ ሂደታቸውን በዝርዝር የመገምገምና ጉድለቶች እንዲፈቱ የሚያስችሉ ተግባራትን የሚያካትት መሆኑን የጠቆሙት ዳይሬክተሩ በዚህም መሰረት በከተሞች ፕላን ትግበራ ዘርፍ ለ20 የገጠር አገልግሎት ማዕከላት እንዲሁም ለ19 ከተሞች የቅየሳ ነጥቦች በማንበብ ፕላን ወደ መሬት እንዲወርድ የቴክኒክ ድጋፍና ክትትል ለማድረግ ታቅዶ በቤንች ሸኮ ዞን 9፣ በኮንታ ዞን 8፣ በምዕራብ ኦሞ ዞን 6፣ በሸካ ዞን 6፣ በካፋ ዞን 4 በድምሩ ለ41 የገጠር ማዕከላትና ከተሞች ድጋፍ ማድረግ ተችሏል ያሉት አቶ ፀጋዬ ለ12 የገጠር አገልግሎት ማዕከላት እንዲሁም ለ16 ከተሞች ፕላን ትግበራ ቅየሳ ማናበቢያ ተከላና መረጃ ማደራጀት ስራ ታቅዶ በምዕራብ ኦሞ ዞን 5፣ ኮንታ ዞን 2፣ ቤንች ሸኮ ዞን 9፣ ዳውሮ ዞን 8፣ ሸካ ዞን 2 እና ካፋ ዞን 1 በድምሩ ለ27 የገጠር ማዕከላትና ከተሞች ላይ ማሳካት ተችሏል ብለዋል።
የፕላን ጥሰት የህግ መሰረት የሌለው የመሬት አጠቃቀም ለውጥ እንደሆነ ጠቅሶ አስቀድሞ በተዘጋጀ የከተማ ፕላን ዕቅድ መሠረት የተደረጉ የተለያዩ የመሬት አጠቃቀም ምድቦች ሆኖ በተለያዩ ምክንያቶች ይህ የመሬት አጠቃቀም በጥብቅ ዲሲፕሊን የማይከወን ሲሆን ሊኖር የሚችል ነባራዊ ሁኔታ ነው ያሉት ዳይሬክቴሩ ከዚህም መነሻ የፕላን ትግበራ ሂደት ግምገማ በተደረገባቸው 7 ከተሞች ላይ የፕላን ጥሰቶችን በመለየትና ግብረመልስ በመስጠት የእርምት እርምጃ እንዲወሰድ ክትትል ለማድረግ ታቅዶ በ9 ከተሞች ማለትም ከካፋ ዞን 4፣ ከኮንታ ዞን 1፣ ከዳውሮ ዞን 2፣ ከሸካ ዞን 1፣ ከምዕራብ ኦሞ ዞን 1 ከተሞች ላይ ተግባሩ ተከናውኗል ብለዋል።


በ16 የገጠር አገልግሎት ማዕከላት ነዋሪዎች በከተሜነት ማስፋፋት ላይ ግንዛቤ ለመፍጠር ታቅዶ በምዕራብ ኦሞ ዞን 6፣ ቤንች ሸኮ ዞን 5፣ ካፋ ዞን 3፣ ዳውሮ ዞን 2፣ ኮንታ ዞን 2፣ ሸካ ዞን 1 በድምሩ ለ19 የገጠር አገልግሎት ማዕከላት ነዋሪዎች ግንዛቤ መፍጠር ተችሏል እንደተቻለ ነው አቶ ፀጋዬ የጠቆሙት።
በበጀት ዓመቱ የታቀዱ ተግባራት በአብዛኛው ስኬታማ ቢሆኑም የከተማ ፕላን ከዝግጅት ባሻገር ትግበራው ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባ በአጽንኦት የተናገሩት ዳይሬክተሩ የዘርፉ ባለሙያዎች እጥረት፣ የፕላን ዝግጅትና ትግበራ ባለሙያ የሌላቸው ዞኖች መኖር፣ የከተማ ወሰን ማካለል ተግባር በወቅቱ አጠናቆ ለፕላን ሥራ ምቹ ያለማድረግ፣ ተናቦ ያለመስራትና ክትትልና ድጋፍ ማነስ፣ ለከተማ የህብረተሰብ ተሳትፎ አደረጃጀት ስራዎች የሚሰጠው ትኩረት መቀዛቀዝ ለሥራዎች ማነቆዎች እንደሆኑም አስረድተዋል።
በከተሞች ጤናማ የፉክክር ስሜትን በመፍጠር ከተሞችን በፕላን መምራት፣ ለማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴዎች የተመቹ በምሳሌነት ሊጠቀሱ የሚችሉ ለማድረግ በርካታ ተግባራት ማከናወን ስለሚገባ በየደረጃው ያሉ አካላት የተቀናጀ ርብርብ እንዲያደርጉ የኢንስቲትዩቱ ዳይሬክተር አቶ ፀጋዬ ኃይሌ ጥሪ አቅርበዋል።


በፍቅር ከበደ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *