




በሀገር አቀፍ በ2017 ዓ.ም በመትከል ማንሰራራት በሚል መሪ ቃል እየተካሄደ የሚገኘው የአረንጓዴ አሻራ መርሀግብር አካል በድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር ተጀምሯል።
በመርሐግብሩ ላይ የስራና ክህሎት ሚኒስትር ሙፈሪሃት ካሚል፤ የዋና ጽ/ቤት፣ የክልልና የከተማ አስተዳደር ቅርንጫፍ ጽ/ቤቶች አመራሮችና የከተማ አስተዳደሩ ከፍተኛ አመራሮች ተገኝተው አሻራቸውን አኑረዋል።
የብልፅግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዚዳንትና የዋና ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ አደም ፋራህ በድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር የአረንጓዴ አሻራ መርሀግብር ባስጀመሩበት ወቅት እንደተናገሩት፤ በመትከል ማንሰራራት በሚል መሪ ቃል በአገር አቀፍ ደረጃ እየተካሄደ የሚገኘው የአረንጓዴ አሻራ መርሀግብር በላቀ ውጤት እየተፈፀመ ይገኛል።
የአረንጓዴ አሻራ መርሀግብር የአየር ንብረት ለውጥ በመቆጣጠር፣ የግብርና ምርታማነት በመጨመር፣ ስራ ዕድል በመፍጠር፣ የአካባቢ ውበት በማስተካከል ጉልህ ሚና አያበረከተ መሆኑን ገልጸዋል።
በአረንጓዴ አሻራ ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ ያላቸውና ለአካባቢው ተስማሚ የሆኑ ችግኞች እየተተከሉ በሁሉም አካባቢዎች በውጤታማነት እየተካሄደ ይገኛል ብለዋል።
መላው ህዝብ በልዩ ትኩረት የድርሻውን በመወጣቱ ምስጋና ይገባዋል ብለዋል አቶ አደም ፋራህ።
በአረንጓዴ አሻራ መርሀግብር ኢትዮጵያ ለአለም የተምሳሌትነት ሚና እየተጫወተች መሆኗንም አንስተዋል።
ድሬዳዋ ካላት የአየር ንብረት ፀባይ አኳያ የአረንጓዴ አሻራ መርሀግብር ከፍተኛ ፋይዳ አለው ብለዋል።
ከተማ አስተዳደሩ በመርሀግብሩ ያስመዘገበውን ተሞክሮ አጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት አሳስበዋል።
