የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልልን ምን ያህል ያውቃሉ?

Spread the love

የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልልን ምን ያህል ያውቃሉ?

ባለፉት ተከታታይ ወራት ‘’የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልልን ምን ያህል ያውቃሉ?’’ በሚል አምድ አጠቃላይ የክልሉን ገጽታ የሚያሳዩ እና የስድስቱ ዞኖች የተለያዩ ባህላዊ ይዘቶችን የዳሰሱ ጽሁፎችን እንደየቅደምተከተላቸው ለውድ አንባቢያን አጋርተናል፡፡

በተመሳሳይ ዛሬ ደግሞ በዚሁ አምድ”በኮንታ ዞን የሚገኙ የኦሽካ ዴንቻ ማኅበረሰብ ባህላዊ የብረት ማቅለጫ ዘዴን ሊናስቃኛችሁ እንወዳለን።

ሀገራችን ኢትዮጵያ ጥንታዊ አገር በመሆኗ የሀገር በቀል እዉቀቶችና ልምዶች ያላት፣ረጅም ዘመናትን ያስቆጠሩ የብዝሃ ቋንቋ፣ ባህሎች፣ ማንነቶች ዳብረዉ ያሉባት ሀገር ናት።

የሰው ልጅ እዚህ ዓለም መኖር ከጀመረ ብዙ ሺህ ዓመታትን አስቆጥረዋል። በዚህ ሁሉ ዘመን እያንዳንዱ ትውልድ የሚኖርበትን አከባቢ ተፈጥሮ ባደላቸው የዕውቀት ችሎታና በየገጠመኞች ባከማቸው ልምድ እየታገዘ መሠረታዊ የሆኑትን ፍላጎቶቹን ለማሟላት ከፍተኛ ጥረት በማድረግ ላይ ይገኛል፡፡

እነዚህን ዕውቀቶች ፣ ክህሎት እና የፈጠራ ውጤቶችን በየጊዜው እያሻሻሉና በውጤቱም እየተጠቀሙ ከትውልድ ወደ ትውልድ ሲያሸጋግሩ ኖረዋል።

አብዛኞቹ ልምዶችና እውቀቶች የሰው ልጅ በዚህ ምድር ላይ ሲኖር ተፈጥሮ የምታደርስበትን ተፅዕኖ አሸንፎ ካልሆነም ተቋቁሞ ለመኖር የሚያደርጋቸው ጥረት ውጤቶች ናቸው፡፡

ስለዚህ ሀገራችንን ጨምሮ በአለም ላይ ያሉ ሀገሮች ሁሉም ለዕድገትና ለዘላቂ ልማት በሚያደርጉት ትግል ውስጥ ባህላዊ የሆኑትን ሀገር በቀል ዕውቀቶችንና ክህሎቶች ጥቅም ላይ በማዋል እንደመነሻ ይጠቀሙባቸዋል፡፡

እነዚህ እውቀቶች ከብዙ ሺህ ዓመታት በፊት ጀምሮ ሲወርድ ሲዋረድ ተጠብቀው እዚህ ዘመን የደረሱ ናቸው፡፡

በሀገራችን ኢትዮጵያ በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል በኮንታ ዞን ካሉ በርካታ ሀገር በቀል እውቀቶችና ልምዶች የኦሽካ ዴንቻ ማኅበረሰብ ባህላዊ የብረት ማቅለጫ ዘዴ አንዱ ነው።

ኦሽካ ዴንቻ በክልላችን ከሚገኙ ከስድስቱ ዞኖች በኮንታ ዞን ኮንታ ኮይሻ ወረዳ ውስጥ የሚገኝ ቀበሌ ነው። ቀበሌውም ከዞኑ ዋና ከተማ አመያ ከ123 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ይገኛል። በቀበሌዉም ጻራ በመባል የሚታወቁ ማህበረሰብ ክፍሎች ይገኙበታል።

ኦሽካ ዴንቻ ከፍተኛ የብረት ማዕድን ክምችት ያለበት አከባቢ ሲሆን በአካባቢዉ የሚኖሩ የጻራ ማህበረሰቦች ለዘመናት ባከማቹት ልምድ በባህላዊ መንገድ ብረትን በማቅለጥ ለተለያዩ እርሻ መሳሪያ፣ለቤት ዉስጥ መገልገያ ቁሳቁሶችና ለጌጣጌጦች ይጠቀሙበታል።

በዞኑ ኮንታ ኮይሻ ወረዳ ኦሽካ ዴንቻ በሁለት ቀበሌዎች ላይ በ4,000 ሺህ ሄክታር መሬት ላይ ያረፈው የኦሽካ ዴንቻ የብረት ማዕድን ክምቸት ይገኛል ፡፡

በኦሽካ ዴንቻ የሚገኙ የጻራ ማህበረሰቦች በሀገር በቀል እዉቀትና በልምድ ባገኙት ክህሎት የተካኑ ናቸዉ። እነዚህን ማኅበረሰቦችን ልዩ የሚያደርጋቸው ተፈጥሮን በባህላዊ መንገድ የመለየት/የማወቅ ጥበብ አላቸዉ።

እነዚህ ማኅበረሰቦች በአከባቢው ያለው የብረት ማዕድን ክምችትን በባህላዊ መንገድ በመለየት ከመሬት ቆፍረው በማውጣትና በማቅለጥ ለተለያዩ እርሻ መሳሪያ፣ለቤት ዉስጥ መገልገያ ቁሳቁሶችና ለጌጣጌጦች ይጠቀሙበታል።

ጻራዎች የብረት ማዕድንን ከአፈር ውስጥ ቆፍረው ከማውጣታቸው በፊት በአካባቢው ብረት መኖሩንና አለመኖሩን ለማረጋገጥ ጉድጓድ ይቆፍሩና በደረታቸው ተኝተው ጆሮአቸውን በተቆፈረው ጉድጓድ ላይ ተክለው ያዳምጣሉ፡፡

በመቀጠልም የብረት ማዕድን መኖሩን ካረጋገጡ በኋላ ሹል እንጨት በመሰካት ምልክት አድርገው ያልፋሉ፡፡ በዚህም የተወሰነ ርቀት ከተጓዙ በኋላ በአንድ ዛፍ ጥላ ስር ተሰባስበው ይወያያሉ፡፡ የውይይታቸው አላማም አፈር የመለየት ስራ ለመሥራት ነዉ።

ማኅበረሰቡ ረጅም ጊዜ ያካበተውን ልምድ ተጠቅሞ በአከባቢው የብረት ማዕድን መኖሩን ካረጋገጠ በኋላ ቆፍሮ በማውጣት ለማቅለጫነት ታስቦ በተሠራው ትልቅ እንስራ ውስጥ ማዕድኑንና ከሰል ቀላቅለው በመጨመር ወናፍ በመጠቀም ተራ በተራ በህብረት እየነፉ እንስራ ውስጥ የተጨመረውን የብረት ማዕድን በከፍተኛ ሙቀት በመቀቀል ወደ ንጹሕ ብረትነት ይቀይራሉ።

ይኽንን ንጹህ ብረት በእሣት አጋግሎ በመቀጥቀጥ የተለያዩ ስለታም መሣሪያዎች ማለትም ቢላ፣ ጦር ፣ የእርሻ ማረሻ ፣ በእግር የሚደረጉ ጌጣጌጥ ፤ ሰይፍ፤ የትንፋሽ መሣሪያ፤ መጥረቢያ እና ሌሎች እቃዎችን በመስራት ለራሳቸው ከመጠቀም አልፎ ወደ ገበያ አውጥቶ በመሸጥ ገቢም ያገኛሉ ኢኮኖሚያቸውንም ያሻሽላሉ።

የኦሽካ ዴንቻ ማኅበረሰብ ባህላዊ ብረት ማቅለጫ ዘዴ የሀገር በቀል እውቀትን የቀደምት አያቶች ፈጥረው ጠብቀው እንዲሁም እየተጠቀሙ ለአሁኑ ትውልድ ያስተላለፉት ትልቅ ሀብት ነዉ።

ይህንን ሀገር በቀል እውቀት መጠበቅ፣ ማልማትና ጥቅም ላይ የሚውልበትን መንገድ መቀየስና ተግባራዊ ማድረግ ከአሁኑ ትውልድ የሚጠበቅ ተግባር ነው።

ምናልባትም በአከባቢው የሚገኘው እምቅ የተፈጥሮ የብረት ማዕድን ክምችት ሀብት በቴክኖሎጂ ታግዞ ወደ ማምረት ቢገባ የአከባቢው ማህበረሰብ ተጠቃሚነት ከማረጋገጥ ባሻገር የሀገሪቱን ኢኮኖሚ ያነቃቃል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *