




የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ሠላምና ፀጥታ ቢሮ ወሳኝ ኩነቶች ምዝገባ ዘርፍ ከክልሉ ጤና ቢሮ ጋር በቅንጅት በተሰሩ የ2017 በጀት ዓመት የአፈጻጸም ግምገማ መድረክ በቦንጋ እያካሄደ ይገኛል።
በመድረኩ ላይ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የክልሉ የመንግሰት ረዳት ተጠሪ አቶ በላይ ተሰማ እንደሀገር ሁለንተናዊ ብልጽግና ለማረጋገጥ በተሰሩ ስራዎች ለውጥ እየተመዘገበ መሆኑን አንስተው ለስኬቱ ቀጣይነት መረጃን ማዘመን ወሳኝ መሆኑን ገልጸዋል።
አክለውም በሁሉም ዘርፍ የዜጎችን ተሳትፎ እና ፍትሐዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ መረጃውን ማዘመንና በቴክኖሎጂ ማስደገፍ ሚናው የጎላ መሆኑን በማስታወስ ለዚሁም መንግስት በፋይዳ የዲጂታል መታወቂያ ላይ እየሰራ ያለውን ተግባር ለአብነት አንስተዋል ።
በመሆኑም ለሰራው ስኬታማነት መንግስት አስፈላጊውን ግብዓት የማሟላትና ስርዓትን ለመዘርጋት ዘርፌ ብዙ ተግባራትን እያከናወነ በመሆኑን ተናግረዋል።
መረጃ ለፖሊስ አውጪዎች እንደ ግብዓትነት የሚያገለግል በመሆኑ የመረጃ ስርዓትን የማጠናከር ጉዳይ በአንድ ተቋም ብቻ የሚሳካ ባለመሆኑ የባድርሻ አካላት ኃላፊነታቸውን በአግባቡ እንዲወጡ አሳስበዋል።
የእንኳን ደህና መጣችሁ መልዕክት ያስተላለፉት የክልሉ ሠላምና ፀጥታ ቢሮ ምክትል ኃላፊና የወሳኝ ኩነቶች ምዝገባ ዘርፍ ኃላፊ አቶ ሠለሞን ደነቀ የሀገራዊ ራዕን ዕውን ለማድረግ የዜጎች ማንነትን በአስተማማኝ የህግ ማዕቀፍና በቴክኖሎጂ አሠራር ስርዓት በመዘርጋት መዝግቦ መያዝ ወሳኝ መሆኑን ገልጸዋል።
ከዓለምአቀፉ ማህበረሰብ ጋር ያለውን ግንኙነት ዘመናዊና ቀልጣፋ ለማድረግ የመረጃ ሚናው የጎላ መሆኑን ጨምረው ገልጸዋል።
የወሳኝ ኩኔት መረጃ የ2030 ዘላቂ የልማት ግቦችን ለማሳካት ከማገዙም ባሻገር የእናቶችና ጨቅላ ህፃናት ሞትን ለመቀነስ፣ ድህነትን ለማስወገድ እንዲሁም የአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖዎች/አደጋዎችን ለመቋቋም እና አቅም ለመገንባት መረጃውን በአግባቡ ማደራጀት አስፈላ መሆኑን ጠቅሰዋል።
ለስኬታማነቱ በክልሉ በ2017 ዓ/ም ከ930 ቀበሌዎች በ703 የዲጂታል ምዝገባ መካሄዱን በመጥቀስ በያዘነው በጀት ዓመት ወደ 865 ለማድረስ ታቅዶ እየተሰራ መሆኑን በመግለፅ በክልሉ በሚገኙ በ11 ሆስፒታል እና በ45 የጤና ጣቢያዎች የሞትና ልደት ምዝገባ በቅንጅት እየተካሄደ መሆኑን ተናግረዋል።
በመሆኑም የሲቭልና የቤተሰብ ምዝገባ ስርዓት በአንድ አካል ተጀምሮ የሚጠናቀቅ ባለመሆኑ ሁሉም ባለድርሻ አካላት በህግ የተሰጠውን ኃላፊነት በጋራና በግል ስወጣ መሆኑን ጠቁመዋል።
ለተሳታፊዎች በ2017 ዓ/ም በተፈጸሙ ተግባራት ዙሪያ የተደረገ የድጋፊና ክትትል ግብረ መልስ በወሳኝ ኩነት ዘርፍ የትምህርትና ስልጠና ዳይሬክተር በሆኑት በአቶ ኃ/ሚካኤል ፎጊ እየቀረበ ይገኛል።
በመድረኩ ላይ የክልሉ የርዕሰ መስተዳድር ማህበራዊ ዘርፍ አማካሪ ደነቀ ማሞን ጨምሮ የክልሉ ከፍተኛ የመንግስት ስራ ኃላፊዎች፣ በክልሉ ሠላምና ፀጥታ ቢሮ የዘርፍ አመራርና ባለሙያዎች፣ ከዞን የመጡ የጤና መምሪያ ኃላፊዎች፣ የሆስፒታሉ ስራ አስኪያጅ ፣ የተመረጡ የጤና ተቋማት ኃላፊዎችና ሌሎች የባለድርሻ አካላት እየተሳተፉ ይገኛሉ።
በጌታሁን ግርማ
