የፌደራል ስርዓቱን ለማጠናከር እና የፍትህ ስርዓትን ለማሳለጥ የሚያስችል ስምምነት ተፈረመ::

Spread the love

የፌዴሬሽን ምክር ቤት እና የፌዴራል ፍትሕና ሕግ ኢንስቲትዩት የፌደራል ስርዓቱን ለማጠናከር እንዲሁም የፍትህ ስርዓቱን ለማሳለጥ የሚያስችል ስምምነት መፈራረማቸው ተገለጸ።

የፌዴሬሽን ምክር ቤት እና የፌዴራል ፍትሕና ሕግ ኢንስቲትዩት በሕግ የተሠጣቸውን ተግባራትንና ኃላፊነቶችን መነሻ በማድረግ የጋራ ግቦቻቸውን ለማሳካት የሚያስችላቸውን የመግባቢያ ሰነድ ዛሬ በፌዴሬሽን ምክር ቤት ተወያይተው ተፈራርመዋል፡፡

የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባዔ አቶ አገኘሁ ተሻገር በወቅቱ እንዳሉት የተፈረመው ስምምነት ምክር ቤቱ እና የፌዴራል ፍትሕና ሕግ ኢንስቲትዩት በሕግ የተሠጣቸውን ተግባራትን እና ኃላፊነቶችን በጋራ ለማሳካት ያለመ ነው።

በሀብት ማሰባሰብ፣ በአቅም ግንባታ፣ በተግባር ተኮር ጥናትና ምርምር እንዲሁም በመሳሰሉ ጉዳዮች በትብብር መሥራትም የስምምነቱ ሌላኛው አላማ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

አፈ ጉባኤው አክለውም ይህ የመግባቢያ ሰነድ የፌደራል ስርዓቱን ለማጠናከር እና ዘላቂነቱን ለማረጋገጥ፣ የሕገመንግስት ትርጉም ሥራን ለማሳለጥ፣ የፍትህ ስርዓትን በአግባቡ ለመምራት እንደሚያስችል ገልጸዋል።

በክልሎች መካከል መልካም ግንኙነቶችን ለማዳበር ከፌደራል ፍትህ እና ሕግ ኢንስቲትዩት ጋር በቅንጅት መስራት የምክር ቤቱን አፈጻጸም ውጤታማ እንዲሆን ያደርገዋል ብለዋል፡፡

የፌዴራል ፍትሕና ሕግ ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር አምባሳደር ደግፌ ቡላ በበኩላቸው ስምምነቱ የፌዴሬሽን ምክር ቤት በሕገመንግስቱ የተሰጠው ስልጣን እና ተግባር ለኢትዮጵያ ፌደራሊዝም እድገት ከፍተኛ ሚና እንዲጫወት የሚያደርግ መሆኑን ተናግረዋል።

በሕገመንግስት ጉዳዮች እና በክልሎች መካከል ሊኖሩ በሚገቡ የመንግስታት ግንኙነቶች ዙሪያ በጥናት እና የአቅም ግንባታ ሥራን በጋራ መስራት የሚያስችለውን የመግባቢያ ሰነድ በመፈራረማቸው ደስተኛ መሆናቸውንም ገልጸዋል፡፡

ከፊርማ ስነ-ስርዓቱ ቀጥሎ የጋራ የቴክኒክ ኮሚቴ ተቋቁሞና የአፈጻጸም ዕቅድ ተዘጋጅቶለት በአጭር ጊዜ ውስጥ ወደ ተግባር እንዲገባ አቅጣጫ መቀመጡን ከፌዴሬሽን ምክር ቤት የተገኘው መረጃ ያመለክታል ሲል ኢዜአ ዘግቧል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *