የክልሉ መንግስት ለዘላቂ ልማት የልማት አጋር ድርጅቶች ድጋፍ እንዲበረታ ጠየቀ




የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል ርዕሰ መስተዳድር ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ (ዶ/ር) የሕዝብን የኑሮ ሁኔታ ለማሻሻልና ዘላቂ ልማትን ለማረጋገጥ በሚደረገው ጥረት የልማት አጋር ድርጅቶች ድጋፍ እንዲጠናከር ጠይቀዋል።
ርዕሰ መስተዳድሩ ከተለያዩ የተባበሩት መንግስታት ዓለም አቀፍ የልማት አጋር ድርጅቶች የሥራ ኃላፊዎች ጋር በጽ/ቤታቸው ውይይት አካሂደዋል።
በውይይቱ የዓለም ጤና ድርጅት (WHO)፣ የምግብና ግብርና ድርጅት (FAO)፣ የኢንዱስትሪ ልማት ድርጅት (UNIDO)፣ የሰብዓዊ ጉዳዮች አስተባባሪ ቢሮ (OCHA) እና የሕፃናት ፈንድ (UNICEF) የሥራ ኃላፊዎችና ተወካዮች እንዲሁም የክልሉ ከፍተኛ አመራሮች ተሳትፈዋል።
በውይይቱ ርዕሰ መስተዳድሩ በክልሉ የሚገኙ እምቅ የተፈጥሮ ሀብቶች፣ በጤና፣ በትምህርት፣ በአየር ንብረት ለውጥ መቋቋም እየተከናወኑ ያሉ ሥራዎችና ቀጣይ ድጋፍ የሚሹ ዘርፎችን የሚያካትት ዝርዝር መነሻ ጽሁፍ በማቅረብ ውይይት ተደርጓል።
ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ (ዶ/ር) የክልሉ መንግስት የሕዝብን ኑሮ ሁኔታ ለማሻሻል አቅሙ በፈቀደው መጠን ማህበረሰቡን በማስተባበር ከተለያዩ የልማት አጋር ድርጅቶች ጋር በቅንጅት እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
እንዲሁም የልማት አጋር ድርጅቶች የሕዝብን የኑሮ ሁኔታ ለማሻሻልና ዘላቂ ልማትን ለማረጋገጥ ያላቸው ሚና ከፍተኛ መሆኑን ጠቁመው፣ በተለያዩ የልማት አጋሮችና ግብረ-ሠናይ ድርጅቶች በመተባበር በሁሉም ዘርፎች ለውጥ ለማምጣት እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
የልማት አጋር ድርጅቶች ቀጣይ በተለይም የእናቶችና የሕፃናት ሞትን፣ ውሃ-ወለድ በሽታዎችን፣የአየር ንብረት ለውጥ የሚቋቋም ዘላቂ ግብርና በማዘመን የቤተሰብ ምግብ ዋስትና ከማረጋገጥ ባሻገር የቤተሰብ ኢኮኖሚ አቅም ማሳደግ በጤና እና ትምህርት ተቋማት የንፁህ መጠጥ ውሃ አቅርቦት እና ሌሎች የጤና ችግሮችን ለመቀነስ ያልተቋረጠ ድጋፍ እንዲያደርጉ ጠይቀዋል።
በውይይቱ ላይ የዓለም ጤና ድርጅት የኢትዮጵያ ተወካይ ዶ/ር ፍራንሲስ ቺሳካ ካሶሎ የልማት አጋር ድርጅቶች በተለያዩ የአፍሪካ ሀገራት ያላቸውን ተሞክሮዎች በኢትዮጵያ እና በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል ለማስፋፋት በተናጠልና በተቀናጀ መልኩ ይሰራል ሲሉ ገልጸዋል።
በፍቅር ከበደ
