በክልሉ የሚገኙ የሚዲያ ተቋማት የተደራጀ ወቅታዊ፣ ቀልጣፋና ውጤታማ መረጃዎችን ለኅብረተሰቡ ማዳረስ ይቻሉ ዘንድ ድጋፋዊ ክትትል እየተደረገ እንደሚገኝ የክልሉ የመንግሥት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ አስታወቀ



እንደሚገኝ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል የመንግሥት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ በታርጫ ከተማ የሚዲያ ፎረም ውይይት እያካሄደ ይገኛል።
በፎረሙ የተገኙ የቢሮው ኃላፊ አቶ የሺዋስ ዓለሙ እንደተናገሩት ተቋማቱ በክልሉ መንግሥት የሚከናወኑ የልማት ተግባራትን በማስተዋወቅ ረገድ የድርሻቸውን እየተወጡ ሲሆን ይህንን ተግባር አጠናክረው እንዲቀጥሉ የግንኙነት አግባብ ላይ መሥራት ወሳኝ መሆኑንም ተናግረዋል።
እነዚህን በማቀናጀት ተገቢ የሆነ የመረጃ ልውውጥ እንዲኖር የሚያስችል ተግባርም እየተከናወነ ይገኛል።
ሚዲያዎች በክልል ደረጃ እየተከናወኑ የሚገኙ የማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ የልማት ዘርፎች ላይ የሚዲያ ሽፋን ከመስጠት ባለፈ በአገራዊ አጀንዳዎች ዙሪያ እንዲሁም፣ ሕብረ ብሔራዊነት አንድነትን የሚያስተሳስሩ ጉዳዮች ላይ ትኩረት አድርገው መሥራታቸው በጠንካራ ጎን የሚገመገም ስለመሆኑም ተናግረዋል።
በመንግሥትና በሕዝብ መካከል ቀልጣፋና ውጤታማ የመረጃ ልውውጥ እንዲኖርና የሕዝብ አስተያየቶችንና ቅሬታዎችን በማሰባሰብ በተገቢው እንዲፈቱ የማድረግ ሥራ በሚዲያዎች በኩል እየተሠራ እንዳለ የገለጹት ደግሞ በቢሮው ምክትል ኃላፊና የኮሙኒኬሽንና የሚዲያ ግንኙነት ዘርፍ ኃላፊ ዶክተር ወልደማርያም በዛብህ ናቸው።
በቀጣይም የይዘት አካታችነትና ተደራሽነት በጥራትና በስፋት እንዲኖር ለማድረግና በቴክኖሎጂ የተደራጀ የሚዲያ ተቋማትን ለመፍጠር እየተሠራ ስለመሆኑም ገልጸዋል።
የክልሉ የመንግሥት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ በክልሉ በየደረጃው የሚገኙ የመንግሥት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤቶችንና የሚዲያ ተቋማትን ምልከታ በማድረግ ተገቢ የሆነ የዕቅድ አፈጻጸም እንዲኖር የሚያስችል የሚዲያ ፎረም ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም ተገልጿል።
በክልሉ በደቡብ ሬዲዮና ቴሌቪዥን ድርጅት ሥር የሚተዳደሩ አራት ቅርንጫፍ ጣቢያዎች፣ የኢቢሲ ታርጫ ስቱዲዮ፣ የደቡብ ምዕራብ ሚዲያ ኔት ወርክ፣ የከፋ፣ ሸካና ቤንቺ ሸኮ ማኅበረሰብ የቴሌቪዥን ጣቢያዎች፣ በፋና ብሮድካስቲንግ የሚዛን ቅርንጫፍ እና የኢዜአ ቦንጋ ቅርንጫፍ በክልሉ በዋናነት አገልግሎት እየሰጡ የሚገኙ ተቋማት ናቸው።
በክልሉ በ12 ቋንቋዎች የደቡብ ሬዲዮና ቴሌቪዥን ድርጅት ስርጭት እያደረገ ይገኛል።
ሚዲያዎች ዓላማ ተኮር ሥራዎችንም አጠናክረው እንዲሠሩ ተገልጿል።
