በክልላችን የተገነባው ‘ኢቲ’ የማዕድን ልማት አክሲዮን ማኅበር የድንጋይ ከሰል ማጣሪያ ፋብሪካ በቅርቡ ሥራ እንደሚጀምር ተገለጸ

Spread the love

በዳውሮ ዞን ታርጫ ከተማ አቅራቢያ የተገነባው ‘ኢቲ’ የማዕድን ልማት አክሲዮን ማኅበር የድንጋይ ከሰል ማጣሪያ ፋብሪካ በቅርቡ ሥራ እንደሚጀምር ተገልጿል።

የማዕድን ሚኒስትር ዴኤታ ሙሐመድራፊዕ አባራያ፣ የማዕድን ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ብስራት ከበደ እና የኢትዮጵያ ጂኦሎጂካል ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬከተር አቶ ኢጃራ ተስፋዬ፣ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል እና የዳውሮ ዞን የስራ ኃላፊዎች የኢቲ የማዕድን ልማት የድንጋይ ከሰል ማጣሪያ ፋብሪካ ያለበት ሁኔታን ተመልክተዋል፡፡

የኢቲ የማዕድን ልማት ፋብሪካ ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ በፍቃዱ አሰፋ እንደተናገሩት ፋብሪካው በሰዓት 150 ቶን፣ በቀን 3 ሺህ 600 ቶን የታጠበ ከሰል የማምረት አቅም አለው፡፡

ሙሉ በሙሉ ወደ ምርት ሲገባ በኢትዮጵያ የሚገኙ የሲሚንቶ ፋብሪካዎችን የታጠበ ከሰል ፍላጎት 75 በመቶ የመሸፈን አቅም እንዳለውም ዋና ስራ አስኪያጁ ገልጸዋል።

አሁን ላይ ፋብሪካው አስፈላጊ የሚባሉ ማሽኖች ተገጥመውለት በመጠናቀቅ ላይ እንደሚገኝ ጠቁመው በፋብሪካው የሚሠሩ ቋሚ ሠራተኞች ሥልጠና ወስደው የሙከራ ሥራዎች እየተሰሩ መሆኑንና በቅርቡ ተመርቆ ሥራ እንደሚጀምር አስታውቀዋል፡፡

ፋብሪካው በጥቂት የውጪ ሀገር እና የሀገር ውስጥ ሠራተኞች እየተገነባ መሆኑ ለሀገር ውስጥ ባለሙያዎች ልምድ መካበት የበኩሉን አስተዋፅዖ ያበረክታል ነው ያሉት።

ኢትዮጵያ በቂ የድንጋይ ከሰል ማዕድን ያላት ቢሆንም የድንጋይ ማጣሪያ ፋብሪካ ባለመኖሩ በውጭ ምንዛሪ ገዝታ የታጠበ ከሰል እንደምታስገባ መግለጻቸውን ከማዕድን ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያመላክታል፡፡

ፋብሪካው በኢትዮጵያ የሚገኙት አምራች ኢንዱስትሪዎች(በተለይ የሲሚንቶ ፋብሪካዎችን) የሃይል ፍላጎት ለማሟላትና ብሎም ከውጭ የሚገባውን የከሰል ምርት በመተካት ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዳለውም አመላክተዋል፡፡

የውጭ ምንዛሪ በማዳንና የግብዓቱን አቅርቦት አስተማማኝና ቀጣይነት ያለው በማድረግ ለኢኮኖሚያዊ እድገት የላቀ አስተዋፅዖ ይኖረዋል ሲሉም ዋና ስራ አስኪያጁ መናገራቸው ተጠቁሟል ሲል የዘገበው ኢዜአ ነው።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *