“ሪፖርታዥ”

Spread the love

በሀገር ደረጃ ከተነደፉ የተቋማት ማሻሻያ ፕሮግራሞች ውስጥ አንዱ መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት ነው።

የለውጡ መንግስት ልዩ ትኩረት ሰጥቶ ከሰራባቸው ጉዳዮች መካከል አንዱ የሆነው የመሶብ አንድ ማዕከል አገልግሎት የመንግስት ተቋማት አገልግሎትን አሰጣጥ በማሻሻል የዜጎችን የአገልግሎት ፍላጎት ማርካትን ዕውን ማድረግ መሆኑ ይታወቃል፡፡

በደቡብ ምዕራብ ክልል የመሶብ አንድ ማዕከል አገልግሎት በሚዛን ብዝሃ ማዕከል አማን ከተማ ተገንብቶ ከጥቅምት 24/2018 ዓ.ም ተመርቆ አገልግሎት መስጠት መጀመሩ ይታወሳል።

የደቡብ ምዕራብ ክልል የመሶብ አንድ ማዕከል አገልግሎት ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ አስራት አዳሮ፤ በሀገር ደረጃ ሲቪል ሰርቪሱን ሪፎርም ለማድረግ ከተሰሩ ተግባራት አንዱ መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት ነው፡፡

ከዚህ ቀደም ሲል በአገልግሎት አሰጣጥ ላይ የነበሩትን እንግልት፣ ተደጋጋሚ ምልልስና የብልሹ አሰራር ችግሮችን ለመቅረፍ የተዘረጋ ስርዓት ነው ብለዋል።

እነዚህን ችግሮች በመቅረፍ በአንድ በተማከለ ቦታ ላይ ዜጎች የተለያዩ አገልግሎቶች እንዲያገኙ ማስቻል ነው ያሉት አቶ አስራት ይህም ከዚህ በፊት በተበታተነ መልኩ  ይሰጥ የነበረውን የመንግሥት አገልግሎት ወደ አንድ ቦታ የሚሰበሰብ፣ ብልሹ አሰራሮችንና መልካም አስተዳደር ችግርን ይቀርፋል ተብሎ እንደሀገር የተያዘ አቋም መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

በክልሉ የመንግስት ተቋማት የሚሰጡትን አገልግሎት ቀልጣፋ፣ ጥራት ያለው፣ በቴክኖሎጂ የተደገፈ፣ ፍትሃዊ፣ ተደራሽነቱ የተረጋገጠና የዜጎችን የአገልግሎት ፍላጎት የሚያረካና ህዝብ በመንግስት ላይ ፅኑ እምነት እንዲኖረው የሚያደርጉ ስራዎች እየተሰሩ እንደሚገኝ ገልፀዋል፡፡

ይህ ማዕከል ጠንካራ ተቋማትን በመገንባት የታቀዱ አገራዊ የልማት ግቦችን የሚያሳካ፣ የኢትዮጵያን ብልፅግና የሚያረጋግጥ እና ለጠንካራ ሀገረ-መንግሥት ግንባታ መሠረት የሚሆን የመንግሥት አገልግሎትና አስተዳደር ሥርዓት መፍጠር መሆኑን አቶ አስራት ተናግረዋል፡፡

የክልሉ መሶብ ማዕከል አገልግሎት በሚዛን ብዝሃ ማዕከል አማን ከተማ ተመርቆ ወደ ስራ መግባቱንና አገልግሎቱ አምስት ክልልና አራት ፌደራል በአጠቃላይ ዘጠኝ ተቋማት 35 የተለያዩ አገልግሎቶች በተደራጀ መልኩ እየተሰጠ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ማዕከሉ ተመርቆ ወደ ስራ ከተገበባት ጊዜ አንስቶ እስከ አሁን ድረስ ወደ ተቋሙ በአካል መጥተው 16 ሺህ 433 ዜጎች አገልግሎት አገኝተዋል ያሉት አቶ አስራት ከ4 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ተገልጋዮች የኦንላይ አገለግሎት መስጠት ተችሏል ብለዋል፡፡

አሁን ላይ ተቋሙንና ስራውን አገልግሎት ፈላጊ ዜጎች ሚቹ በማድረግ አገልግሎቶችን በዲጂታል አገልግሎት በቴክኖሎጂ የታገዘ የኦን- ላይን አገልግሎት እየሰጠ እንደሚገኝ ነው ዋና ሥራ አስፈጻሚው የተናገሩት።

በዚሁ በመሶብ አንድ ማዕከል አገልግሎት የህብረተሰቡን እርካታ 96.7 ከመቶ ማድረስ የተቻለ መሆንም ተናግረዋል፡፡

ከክልል ቢሮዎች የክልሉ ፍትህ እና ትራንስፖርትና መንገድ ልማት ቢሮዎች አገልግሎት  ወደ አንድ ማዕከል አገልግሎት
በማስገባት በቅርቡ  ለማህበረሰቡ ዲጂታል በሆነ መንገድ አገልግሎት የሚሰጡ መሆኑን አቶ አስራት ጠቁመዋል፡፡

ከዚህ በተጨማሪም በ5 የዞን ከተሞች በቦንጋ፣ ታርጫ፣ ቴፒ እና አመያ ከተሞች እንዲሁም ሚዛን አማን ላይ መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት ግንባታ እየተከናወነ እንደሚገኝና በቅርቡ አገልግሎት መስጠት የሚጀምር መሆኑን ገልጸዋል።

በከንቲባ የሚተዳደሩ  ሌሎች 15 ከተሞችም እንደዚሁ የመሶብ አንድ ማዕከል ግንባታ ስራ በመጀመር ላይ መሆናቸውን ነው  አቶ አስራት  የጠቆሙት። 

በቀጣይ የመንግሥት አገልግሎቶች የህዝብን እሮሮ የሚያስነሱ፣ ብልሹና መልካም አስተዳደር ችግር መነሻ የሆኑ ብዙ ተገልጋይ ያለባቸውን አገለግሎቶችን በሙሉ ወደ መሶብ አንድ ማዕከል እንዲገቡ የማድረግ ስራ ተጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑን አንስተዋል፡፡

ይህ መሶብ አንድ ማዕከል አገልግሎት መንግሥት የህዝብን እንግልት መቀነስ በሚያስችል መልኩ በጥናት ላይ ተመስርቶ ወደ ስራ ከስገባቸው የልማት ኢንሼቲቮች አንዱ እንደሆነ የጠቀሱት አቶ አስራት በዚህም የተበታተነ አገልግሎት በአንድ ቦታ በመሰብሰብ በቴክኖሎጂ በታገዘ አሰራር በመዘርጋት ዜጎች አገልግሎት እንዲያገኙ በማድረግ የታመነ እና ተግባራዊ የተደረገ ነው አቶ አስራት ብለዋል፡፡

የመሶብ አገልግሎት ህዝቡን በርካታ አገልግሎቶችን በአንድ ማዕከል ያለምንም እንግልት የሚያስገኝ አዲስ ሪፎርም አሰራር በመሆኑ ህዝቡም በሚፈልጉበት ጊዜ መጥተው አገልግሎት እንዲያገኙ ዋና ስራ አስፈጻሚው ጥሪ አቅርበዋል።

በተከተል ወ/ሚካኤል

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *