አልሚዎች የወሰዱት መሬት አሟጦ ማልማት ይጠበቅባቸዋል፦ ኢንጅነር ነጋሽ ዋጌሾ (ዶ/ር)

Spread the love

የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ንግድና ኢንቨስትመንት ቢሮ በክልሉ ከሚያለሙ ባለሃብቶች ጋር በመተባበር ያዘጋጁት ክልላዊ ኢንቨስትመንት ፎረም በሚዛን አማን ከተማ ተካሂዷል።

በመድረኩ ማጠቃለያ ሀሳብ የሰጡት የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር እንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ (ዶ/ር)፥ የክልሉ መንግሥት ለንግድና ኢንቨስትመንት ምቹ አጋጣሚዎችን በማመቻቸት ክልሉን የኢንቨስትመንት ማዕከል ለማድረግ ይሰራል ብለዋል።

አልሚዎች በወሰዱት መሬት በተሟላ አቅም ወደ ምርት መግባት እንዳለባቸውም ያሳሰቡት ርዕሰ መስተዳድሩ፥ የአከባቢ ስም ማዕከል ያደረገ የምርት መለያን መጠቀም ይገባል ብለዋል።

“በበሬ የሚያርሱ አልሚዎችን የክልሉ መንግሥት አይታገስም” ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ፥ አልሚዎች ዘመናዊ አሰራሮች በመከተል ምርታማነትን ማላቅ ይገባል ብለዋል።

የመሠረተ ልማት ችግሮችን በባለሀብቶች፣ በማኅበረሰብና በመንግሥት ትብብር መፍታት እንደሚገባ ያሳሰቡት ርዕሰ መስተዳድሩ፥ የክልሉ መንግሥት በዘርፉ የሚገጥሙ ችግሮችን ቀጣይነት ባለው መልኩ ለመፍታት ቁርጠኛ ነው ብለዋል።

በክልሉ የኢንቨስትመንት ፍሰት ለመጨመር እየተከናወኑ ያሉ ተግባራት መጠናከር እንዳለበት ያስገነዘቡት የክልሉ የመንግሥት ተጠሪ አቶ ፍቅሬ አማን፥ አልሚዎች የወሰዱትን መሬት አሟጠው ልማት ላይ ማዋል ይጠበቅባቸዋል ብለዋል።

ለኢንቨስትመንት የተፈቀደውን መሬት በቀጥታ ለአልሚዎች ከማስተላለፍ አኳያ በታችኛው መዋቅር የሚስተዋሉ ችግሮችን በመፍታት የዘርፉን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ማሳደግ እንደሚገባ አስገንዝበዋ።

በቴክኖሎጂ ሽግግር አኳያ የሚስተዋሉ ክፍተቶችን መፍታት እንደሚገባ የገለጹት፥ የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድርና የግብርና ቢሮ ኃላፊ አቶ ማስረሻ በላቸው፥ አልሚዎች በወሰዱት መሬር ከአርሶአደሩ በተሻለ ምርታማነት ማስመዝገብ ይጠበቅባችኋል ብለዋል።

የአግልግሎት አሰጣጥና የመልካም አስተዳደር ችግሮችን በቅንጅት በመፍታት የግሉ ዘርፍ ለዘላቂና ሁሉንአቀፍ የኢኮኖሚ ዕድገት የሚያበረክተው አስተዋጽኦ ማሳደግ እንደሚገባም ነው የክልሉ ንግድና ኢንቨስትመንት ቢሮ ኃላፊ አቶ ታሪኩ አካሉ ያስረዱት።

በየደረጃው ከሚገኙ መዋቅሮች ጋር ተቀራርቦ እየሰሩ መኾናቸውን የገለጹት የመድረኩ ተሳታፊዎች በተላይ ከመሠረተ ልማት እንዲሁም ከአግልግሎት አሰጣጥ ጋር ያሉ ማነቆዎች እንዲፈቱላቸው ጠይቀዋል።

በዕድገቱ በዛብህ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *