




የቡና፣ ሻይና ቅመማ ቅመም ልማትና ግብይት ትስስር እና የኮንትራት እርሻ ውል ማስፈጸሚያ መመሪያ ላይ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና ለባለ ድርሻ አካላት በቦንጋ ከተማ እየተሰጠ ነው።
ስልጠናው የተዘጋጀው አነስተኛ ማሳ ያላቸው የቡና፣ ሻይና ቅመማ ቅመም አምራች አርሶ አደሮችን ከአልሚ ባለሀብቶች ጋር በልማትና ግብይት ትስስር ወይም በኮንትራት እርሻ ውል በማስተሳሰር ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ እንዲሁም የምርት ጥራትን ለማሻሻል ያለመ ነው።
በተጨማሪም ስልጠናው የገበያ ትስስርን በማጠናከር አርሶ አደሮች ምርታቸውን በተመጣጣኝ ዋጋ እንዲሸጡ ምቹ ሁኔታ ለመፍጠር የሚያግዝ ነው።
የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል ቡና፣ ሻይ እና ቅመማ ቅመም ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አስራት መኩሪያ ስልጠናው በክልሉ የቡና፣ ሻይና ቅመማ ቅመም ልማትን ለማጠናከር እና የገበያ ተወዳዳሪነትን ለማሻሻል ትልቅ አስተዋፅኦ እንደሚያበረክት ገልፀዋል።
ከቡና አቅርቦት አንፃር በዓለም አቀፍ ገበያ የሚታዩ ተለዋዋጭ ሁኔታዎች ቢኖሩም በክልሉ የሚገኙ የዘርፉ ተዋናዮች መካከል ትስስርን በማጠናከር ዘርፉን ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገር እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
ዋና ዳይረክተሩ በዘርፉ የቴክኖሎጂ ሽግግርን ማስፋፋት፣ ምርታማነትን ማሳደግ እና ከምርት እስከ ገበያ ያለውን ሰንሰለት በጥራትና በውጤት እንዲመራ ማድረግ አሁንም ትኩረት የሚሻ መሆኑን ጠቁመዋል።
በስልጠናው ለተሳታፊዎች ስለ ኮንትራት እርሻ ውል አፈፃፀም፣ የልማትና ግብይት ትስስር አስፈላጊነት እና የሚጠበቁ ሂደቶች ላይ ዝርዝር ግንዛቤ በዘርፉ ባለሙያ እየተሰጠ ይገኛል።
ስልጠናው የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል የቡና ሻይ እና ቅመማ ቅመም ባለስልጣን ከምግብ ስርዓት ማጠናከሪያ ፕሮግራም ጋር በመተባበር የተዘጋጀ ሲሆን፤ አልሚ ባለሀብቶች፣ የዞንና ወረዳ ባለሙያዎች እና አመራሮች፣ እንዲሁም የክልል ባለድርሻ አካላት በስፋት እየተሳተፉ ይገኛል።
በበረከት ኢዮብ
