የካፋ ዞን ገፅታ
> 2 ሚሊዮን
አሁን የሚገመት የሕዝብ ብዛት
ቦንጋ (Bonga)
የዞኑ ዋና ከተማ
10,602.7 ኪ.ሜ²
አጠቃላይ የቆዳ ስፋት
12 ወረዳ / 5 ከተማ
የአስተዳደር መዋቅር
መልክዓ ምድራዊ አቀማመጥና የአየር ንብረት (Geography & Climate)
የካፋ ዞን በሥነ-ፈለክ አቀማመጥ ከምድር ወገብ በላይ በ 6°24′ – 8°13′ ሰሜን ላቲቲዩድ እና ከግሪንዊች ሜሪዲያን 35°48′ – 36°07′ ምስራቅ ሎንግቲዩድ መካከል ይገኛል።
አጎራባች ወሰኖች፦ በሰሜንና በሰሜን ምስራቅ ከኦሮሚያ ክልል፣ በምዕራብና በደቡብ ምዕራብ ከቤንች ሸኮ ዞን፣ በሰሜን ምዕራብ ከሸካ ዞን፣ እንዲሁም በምስራቅ ከኮንታ ዞን ጋር ይዋሰናል።
የዞኑ ከፍተኛው ቦታ ከባህር ወለል በላይ በጠሎ ወረዳ ውስጥ 3,348 ሜትር ከፍታ ባለው በቶትራ ተራራ ላይ የሚገኝ ሲሆን፣ ዝቅተኛው ደግሞ በደቡባዊ ዲቻ ወረዳ 501 ሜትር ከፍታ ላይ ይገኛል። ዞኑ ሶስት ዋና ዋና የአየር ንብረት ቀጠናዎችን ያቀፈ ነው፡ 70 ሺህ ሄክታር ወይና ደጋ (ከ1300-2200 ሜትር)፣ 22 ሺህ ሄክታር ቆላ (ከ500-1300 ሜትር) እና 8 ሺህ ሄክታር ደጋማ ክፍል (ከ2200-3000 ሜትር)።
በዞኑ አጠቃላይ የቆዳ ስፋት ውስጥ ከ 760 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት የሚሸፍነው የካፋ የተፈጥሮ ጥብቅ ደን፣ በሰኔ ወር 2010 እ.ኤ.አ (June 2010) በዩኔስኮ የዓለም የባዮስፌር ጥብቅ ደን (Biosphere Reserve) ሆኖ ተመዝግቧል። የካፋ ማህበረሰብ ደንን ከጥንት ጀምሮ እንደ አይን ብሌኑ ተንከባክቦ ከልጅ ወደ ልጅ በባህላዊ መንገድ እያሸጋገረ የመጣበት ታላቅ የጋራ ገፀ-በረከት ነው።
የካፋ መንግሥት ታሪክና የሚክሬቾ ሥርዓት (History & Governance)
የካፋ ማህበረሰብ የራሱ የሆነ ጥንታዊ፣ ረቂቅና የዳበረ የንግሥና እና የምክክር ሥርዓት የነበረው ታሪካዊ ህዝብ ነው። ታሪካዊ ጥናቶች እንደሚያመለክቱት የካፋ የንግሥና ዘመን በሶስት ዋና ዋና ስርወ-መንግስታት የተመራ ነበር። እነሱም፦ ማንጆ፣ ማቴ እና ሚኖ ስርወ-መንግስታት ናቸው። የካፋ የንግሥና ስልጣን ከአባት ወደ ልጅ በውርስ የሚተላለፍበት የዳበረ የስልጣን መዋቅር ነበረው።
የሚክሬቾ (የምክር ቤት) አደረጃጀት፦ ንጉሱን በማማከርና በመደገፍ ረገድ ወደ አስር የሚጠጉ የተለያዩ የስልጣን ደረጃዎች ያሏቸው የምክር ቤት (ሚክሬቾ) አባላት ነበሩት። ይህም መዋቅር አሁን ያለውን ዘመናዊ የአስተዳደር ስነ-ስርዓት የሚከተል ሆኖ ከንጉሱ ቀጥሎ ጉጄራዎች፣ ካተማራዎች፣ ወፈራዎች፣ አርችየራዎች እያለ ወደ ታችኛው እርከን የሚወርድ የተዋቀረ የባለስልጣናት ሰንሰለት ነበረው።
ቡና እና ካፋ፡ የማይነጣጠሉ ታሪካዊ ቁርኝት (The Birthplace of Coffee)
ካፋ በዓለም አቀፍ ደረጃ የቡና መገኛ ምድር (የአረቢካ ቡና ምንጭ) ለመሆኑ የታሪክ መጻሕፍትና ማረጋገጫዎች ያሰረዱታል። “ቡና” ለሚለው የእንግሊዝኛ ቃል (Coffee) መጠሪያነት መነሻ የሆነው “ካፋ” ከሚለው የዞኑ ስም ተወስዶ እንደሆነ ይነገራል። ቡናን ለመጀመሪያ ጊዜ ያገኘው “ካልዲ” የተባለ የፍየል እረኛ እንደነበር በታሪክ ተመዝግቧል።
ይህንን ታሪካዊና አለም አቀፋዊ የካፋና የቡና ቁርኝት በተግባር ለዓለም ለማሳየትና ቅርሱን ጠብቆ ለማቆየት ሲባል በቦንጋ ከተማ እጅግ ዘመናዊ ብሔራዊ የቡና ሙዚየም ተገንብቶ በአሁኑ ወቅት በቦንጋ ዩኒቨርሲቲ አማካኝነት እየተስተዳደረ በርካታ ምርምሮችና ተግባራት እየተከናወኑ ይገኛሉ።
ባህላዊ እሴቶች፣ አለባበስና የአመጋገብ ስርአት (Culture & Gastronomy)
የካፋ ዞን በውስጡ ሶስት ነባር ብሔረሰቦችን ማለትም ካፋ፣ ናይ እና ጻራ ብሔረሰቦችን አቅፎ የያዘ፣ እርስ በእርስ ተከባብረውና ተደጋገፉ የዘመናት የታሪክ ትስስር ያላቸው ማህበረሰቦች የሚኖሩበት ቀጠና ነው። የጋራ አንድነታቸውንና ፍቅራቸውን የሚገልጹበት ልዩ መገለጫ “ዳጎ” ይባላል፤ ይህም ሁለት ሆነው በአንድ እቃ ላይ አፋቸውን ገጥመው የሚጠጡበት የአብሮነት ስርዓት ነው።
የእንሰት ባህላዊ ምግብ፦ እንሰት በካፈቾዎች ዘንድ ታላቅ ቦታ የሚሰጠው ተክልና የደህንነት ዋስትና ነው። ዋናው ባህላዊ ምግባቸው ሲሆን ከእንሰት በርካታ የምግብ አይነቶች ይዘጋጃሉ። እንሰት ተፍቆ ቆጮ፣ ኤትኖ፣ ዱፖ ሲወጣ፣ የእንሰቱ ስር (ቂጡ) ተቀቅሎ “አምቾ” ተብሎ ይቀርባል። ማባያ አድርገው አይብ፣ ቅቤ፣ ሱፍና ወተት ያዘወትራሉ።
ባህላዊ አለባበስና ስነ-ስርዓት፦ የካፈቾ ባህላዊ የአለባበስ ዘይቤ በካፋ ባንዲራ ቀለማትና ምልክት ተመስሎ በተለያዩ ድንቅ ዲዛይኖች የሚዘጋጅ ሲሆን፣ ባህላዊ ልብሱ ላይ ጋቢ ተደርቦ ይለበሳል። በደስታ ጊዜ (ጋብቻ፣ ቤት ምርቃት) ልዩ የደስታ ጭፈራዎች ያሉ ሲሆን፣ በለቅሶ ጊዜ ማህበረሰቡ ተሰብስቦ “ህቾና ጎሞ” የሚባሉ የሀዘን መግለጫ ትዕይንቶችን በማሳየት ተበዳይንና አልቃሾችን ያጽናናሉ።
Nation and nationalities in Kafa Zone, Kafecho, Na’o and Chara

Kafa Nation

Na’o Nationality

Chara Nationality



















