
የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ከሥር መዋቅሮችና ከባለድርሻ አካላት ጋር የ2018 በጀት ዓመት ዕቅድ አፈፃፀምና የ2019 ዕቅድ የግምገማ መድረክ በሚዛን አማን ከተማ እየተካሄደ ይገኛል፡፡
የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት ክቡር አቶ ቆጭቶ ገብረማርያም በመድረኩ ባደረጉት መክፈቻ ንግግር የዳኝነት አገልግሎት ለሁሉም ተደራሽ በማድረግ በክልሉ ዘላቂ ሰላምን ማፅናትና ልማትን የማፋጣን ስራ ከፍተኛ ትኩረት ተደርጎ እየተሰራ እንደሚገኝ ገልፀዋል።
በ2018 በጀት ዓመት በክልሉ ቀልጣፋ፣ ፍትሐዊ፣ወጭ ቆጣቢና ተደራሽ የዳኝነት አገልግሎት ለሁሉም እኩል ለመስጠት ሰፊ ስራዎች ተሰርተዋል ያሉት አቶ ቆጭቶ ገ/ማሪያም የዳኝነት አገልግሎት አሰጣጥ ቅልጥፍናንና ዉጤታማነትን በማሳደግ፣ የዳኝነት ነፃነት እና ተጠያቂነት በማረጋገጥ ፣ የአገልግሎት ተደራሽነትን ማስፋት መቻሉን ጠቁመዋል።
ማህበራዊ ፍርድ ቤቶችና ባህላዊ ፍርድ ቤቶች የዳኝነት ስርዓቱን ቀልጣፋ፣ተደራሽና ወጭ ቆጣቢ እያደረገ በመሆኑ ለህብረተሰቡ በጣም ጠቃሚ በመሆናቸው ቅንጅታዊ አሰራር በማጠናከር ተደራሽነታቸውን ማስፋፋት ያስፈልጋል ብለዋል።
በበጀት ዓመቱ በወንጀል እና ፍትሃብሔር ከቀረቡ 62 ሺህ 722 መዘገቦች መካከል 61 ሺህ 20 መዝገቦች ላይ ውሳኔ መስጠት መቻሉን ክቡር አቶ ቆጭቶ አክለው ገልፀዋል።
በዚህም ቀሪ 1 ሺህ 702 መዝገቦች ወደ ቀጣይ በጀት ዓመት በቀጠሮ መተላለፋቸዉን የተጠቆመ ሲሆን የፍርድ ቤት ጉዳዮችን በተቀመጠዉ ጊዜ ሠሌዳ ዉስጥ የመወሰን አቅምን እያደገ መምጣቱን ነው የገለፁት::
የተክኖሎጂ ስርፀት ወጥነትን በማረጋገጥ፤አልፎ አልፎ የሚታዩ የመልካም አስተዳደርና የስነምግባር ግድፈቶችን በማረምና ቅንጅታዊ አሰራሮችን በማጠናከር የህብረተሰቡን የፍትህ ጥማት ማርካት አሁንም ትኩረት ተሰጥቶት ይሰራል ብለዋል።
ለተከታታይ ሁለት ቀናት በሚካሄደው ጉባኤ በአፈጻጸም ግምገማው የታዩ ክፍተቶች ቀጣይ አቅጣጫዎች ዙሪያ ሰፊ ምክክር ይደረግበታል ተብሎ ይጠበቃል።
