Trendings

የቆላማ አካባቢዎችኑሮ ማሻሻያ ፕሮጀክት ሁለተኛ ምዕራፍ (LLRP II) የ2019 በጀት ዓመት ዓመታዊ የሥራ ዕቅድ እና የበጀት ትውውቅ የጋራ የምክክር መድረክ እየተካሄደ ይገኛል።

Spread the love

የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል አርብቶ አደርና ቆላማ አካባቢዎች ጉዳይ ቢሮ የቆላማ አካባቢዎች ኑሮ ማሻሻያ ፕሮጀክት ሁለተኛ ምዕራፍ (LLRP II) የ2018 በጀት ዓመት አፈጻጸም ግምገማ እና የ2019 በጀት ዓመት ዓመታዊ የሥራ ዕቅድ እንዲሁም የበጀት ትውውቅ ከክልል፣ ዞን እና ወረዳ ባለድርሻ አካላት ጋር በመካሄድ ላይ ይገኛል።

​በሚዛን አማን ከተማ እየተካሄደ ባለው በዚህ መርሃ-ግብር ላይ የክልሉ አርብቶ አደርና ቆላማ አካባቢዎች ጉዳይ ቢሮ ኃላፊ አቶ መቱ አኩን ጨምሮ የምክትል ቢሮ ኃላፊዎች፣ የፕሮጀክቱ ሥራ አስኪያጅ እና የተለያዩ የትግበራ አካላት ተገኝተዋል።

​በመድረኩ ላይ እንደተገለጸው በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል አርብቶ አደርና ቆላማ አካባቢዎች ሕብረተሰብን ተጠቃሚ ለማድረግ የተለያዩ ፕሮጀክቶች ተቀርጸው ተግባራዊ እየተደረጉ ይገኛሉ ከነዚህም መካከል የቆላማ አካባቢዎች የኑሮ ማሻሻያ ፕሮጀክት ምዕራፍ 2 (LLRP II) አንዱና ዋናው ነው።

​የክልሉ አርብቶ አደርና ቆላማ አካባቢዎች ጉዳይ ቢሮ ኃላፊ አቶ መቱ አኩ በመድረኩ ላይ እንደተናገሩት በተጠናቀቀው በጀት ዓመት አርብቶ አደሩንና ከፊል አርብቶ አደሩን ተጠቃሚ የሚያደርጉ በርካታ ተግባራት ተከናውነው አበረታችና የተሻለ አፈጻጸም ተመዝግቧል።

ኃላፊው አያይዘውም በተጠናቀቀው በጀት ዓመት የተገኘውን ውጤት አስጠብቆ በመቀጠል በአዲሱ በጀት ዓመት የታዩ ክፍተቶችን በግብረ-መልስ በመለየት እና የዕቅዱ አካል በማድረግ ይበልጥ ለውጤታማነት መሠለፍ እንደሚገባ አሳስበዋል።

እንዲሁም ባለድርሻ አካላት ለፕሮጀክቱ ውጤታማነት የየበኩላቸውን ሚና በባለቤትነት ስሜት እንዲወጡ አቅጣጫ አስቀምጠዋል።

​የፕሮጀክቱ ሥራ አስኪያጅ አቶ ደረጀ በቀለ በበኩላቸው በበጀት ዓመቱ በምዕራፍ 2 ተቀርጸው ሥራ ላይ የዋሉ ፕሮግራሞች የተሳካ ውጤት ማስመዝገባቸውን ገልጸዋል። በተለይም ፕሮጀክቱ በምዕራብ ኦሞ ዞን በሚገኙ 4 ወረዳዎች እና በካፋ ዞን 1 ወረዳ በድምሩ በ5 ወረዳዎች ላይ አርብቶ አደሩን ሁለተናዊ ተጠቃሚ የሚያደርጉ የልማት ሥራዎች መከናወናቸውን አብራርተዋል።

​በመድረኩ ላይ የፕሮጀክቱ አፈጻጸም ሪፖርት በአቶ ሳምሶን ክፍሌ የቀረበ ሲሆን የቆላማ አካባቢዎችን ሁለተናዊ ኑሮ ማሻሻል፣ የልማት ሥራዎችን ፍሰት ማቀላጠፍ እና በአዲሱ በጀት ዓመት የሚከናወኑ ዋና ዋና የትኩረት አቅጣጫዎች ላይ ሰፊ ውይይት እየተደረገበት ይገኛል።

የ2019 በጀት ዓመት አጠቃላይ ዓመታዊ የሥራ ዕቅድ ከታችኛው መዋቅር እስከ ክልል ካሉ ባለድርሻ አካላት ጋር በጥልቀት እየተገመገመና ለተግባራዊ ሥራ ዝግጁ እንዲሆን እየተደረገ ነው።የተመደበው በጀት ለታለመለት የልማት ዓላማ በብቃት እንዲውል እና የትግበራ ሂደቱ ግልጽነትና ተጠያቂነት በተሰፈነበት መልኩ እንዲመራ ትኩረት ተሰጥቷል።

እንዲሁም በክልል፣ በዞን እና በወረዳ ደረጃ የሚገኙ ተቋማትና ኃላፊዎች የፕሮጀክቱን አፈጻጸም በቅርበት በመከታተል የተቋቋመውን የልማት ግብ በብቃት ማሳካት እንዳለባቸው ተጠቁሟል።

​መድረኩ በክልሉ የሚገኙ ቆላማ አካባቢዎችን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ገጽታ ለመቀየር የተያዘውን ዕቅድ ወደ መሬት ለማውረድ ጠንካራ መሠረት የሚጥል ሆኖ በባለድርሻ አካላት መካከል ጠንካራ የርክክብና የቅንጅት መንፈስ በመፍጠር ለአዲሱ በጀት ዓመት የተሳካ የሥራ እንቅስቃሴ በር የሚከፍት ሆኖ በቀጣይነት እየተካሄደ ይገኛል ሲል የቤንች ሸኮ ዞን ኮሙኒኬሽን ዘግቧል።

በተለያዩ የማህበራዊ ሚዲያ አማራጮች መረጃዎችን ይከታተላሉን

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *