




አርሶ አደሮቹ በአሁኑ ሰዓት ያመረቱትን ሻይ ለውሽውሽ ሻይ ልማት ድርጅት እያቀረቡ መሆኑንም ጠቁመዋል።
በዞኑ ጊምቦ ወረዳ ምቺቲ ቀበሌ በ1997 ዓመተ ምህረት በ6 አርሶአደሮችና በ6 ሄክታር ማሳ ላይ የተጀመረው የሻይ ልማት ዛሬ አድማሱን አስፍቶ በወረዳው 6 ቀበሌዎችን ከማዳረሱም በላይ በርካታ አርሶ አደሮችን ተጠቃሚ እያደረገ ይገኛል።
ምርት መስጠት ባቆመ አሲዳማ መሬት ሊይ በመተከል ውጤት መስጠት የሚችል ከመሆኑም ባሻገር በአንዴ ተተክሎ ለረዥም ዓመታት አገልግሎት መስጠቱ ከሌሎች ተክሎች ለየት እንደሚያደርገው በዘርፉ የተሰማሩ አርሶአደሮች ለሚዲያችን ገልጸዋል።
በመሆኑም የሻይ ልማት ዘርፍ አዋጭ ነው ያሉት ቀበሌ በልማቱ ከተሰማሩ አርሶ አደሮች መካከል አቶ አለማየሁ አስፋው፣ አቶ ገዛኸኝ ገብሬ እና አቶ ጋዎ ገብሬ በዚህም በልማቱ ከተሰማሩ በኃላ ኑሯቸው ከወትሮው ከመሻሻሉም በላይ ለበርካታ ወጣቶች ስራ ዕድል መፍጠራቸውን ተናግረዋል።
በአሁኑ ሰዓት ማህበራቸው ከ2 ሚሊዮን ብር በላይ ካፒታል ከማስመዝገቡም ባሻገር በየዕለቱ ከ40 ለሚልቁ ወጣቶች ከ5 መቶ ብር በላይ ከፍሎ እያሰራ እንደሚገኝም ጠቁመዋል።
ማህበሩ በአሁኑ ሰዓት የውሽውሽ ሻይ ልማት ድርጅት ጥገኛ ነው ያሉት አርሶ አደሮቹ የአካባቢ ሻይን በ11 ብር እንዲሁም ለውጭ የሚሆን የናሙና ሻይን በ19 ብር ህሳብ እያቀረቡ መሆኑን ጠቅሰዋል።
ይህም በድርጅቱ በጎ ፈቃድ ላይ የተመሰረተ ከመሆኑም ባሻገር በርካታ ምርት እንዲባክን እያደረገ እንደሚገኝ ጠቁመዋል።
በመሆኑም አርሶ አደሮቹ በራሳቸው ፋብሪካ እሴት ጨምሮ በመሸጥ ከሌሎች ጥገኝነት ለመላቀቅ የሚያስችል አነስተኛ የሻይ ማቀነባበሪያ ፋብሪካ ለማቋቋም ፍላጎት እንዳላቸው ገልጸዋል።
በመሆኑም የመንግስት ድጋፍ ልደረግላቸው እንደሚገባም ጠይቀዋል።
በአርሶ አደር ማሳ ተቀጥረው ከሚሠሩ ሠራተኞች መካከል ወጣጥ ገረመው ገባቦ እና ወጣት አብነት አባተ ማህበሩ የተሻለ ስራ ዕድል እንደፈጠረላቸው ገልፀው በዚህም በየዕለቱ ካሽ ገንዘብ እየተከፈላቸው እንደሚሰሩ ገልጸዋል።
ይህም በተሻለ ሁኔታ ከራሳቸው አልፈው ቤተሰባቸውን እንዲረዱ ማስቻሉን የጠቀሱት አስተያየት ሰጪዎቹ ሌሎች ወጣቶችም አልባሌ ቦታ ጊዜ ከማጥፋት በመሰል የስራ ዘርፎች መሰማራት እንዳለባቸው ተናግረዋል።
ሻይ በቂ እንክብካቤ እና ግብዓት ካገኘ ለአርሶ አደሩ ገቢ ማደግና ተጠቃሚነት ወሳኝ ተክል ነው ያሉት በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ቡና፣ ሻይና ቅመማ ቅመም ባለስልጣን የቡናና ሻይ ባለሙያ አቶ ካሳሁን ታዬ በተለይ ለአሲዳማ መሬት ምቹ በመሆኑ ለክልሉ አርሶአደሮች ወሳኝ ነው ብለዋል።
አሁን በሻይ እርሻ ልማት ላይ የተሰማሩ አርሶ አደሮች በአቅራቢያቸው በሚገኙ የሻይ ልማት ድርጅቶች ድጋፍ እንደሚያገኙ የገለጹት አቶ ካሳሁን ቀጥታ ምርቱን ለድርጅቱ እያቀረቡ እንደሚገኝም ተናግረዋል።
በመሆኑም አርሶ አደሮቹ በሂደት አቅማቸው ጎልብቶና በራሳቸው እሴት ጨምረው የሚሸጡበትን ሁኔታ ለመፍጠር አነስተኛ ማቀነባበሪያ ኢንዱስትሪዎችን ከማቋቋም ባለፈ ተወዳዳሪ ባለሀብቶችን በዘርፉ ለማሰማራት ክልል አቅዶ እየሰራ ነውም ብለዋል።
ለዚህም እንዲያመች ለኢንዱስትሪው ግብዓት የሆነውን የሻይ ልማት በአርሶአደሮች ማሳ ለማስፋት ሰፊ እርብርብ እንደ ክልል እየተካሄደ መሆኑንም አቶ ካሳሁን ተናግረዋል ሲል የደቡብ ሚዲየ ኔትወርክ ዘግቧል።
