የተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች ለጠንካራ ሀገር ግንባታ እያደረጉ ያለውን አስተዎጽኦ አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ገለጹ

Spread the love

የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል የተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት በቤንች ሸኮ ዞን እየተሰሩ ያሉ የልማት ሥራዎችን ተዘዋውረው ጎብኝተዋል።

በጉብኝቱ በክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ (ዶ/ር) ሀሳብ አመንጭነት በገበታ ትውልድ መርሃ ግብር የተመረቀው የደንቢ ኢኮ ሎጅን፣ የሚዛን አማን አውሮፕላን ማረፊያ፣የደቡብ ምዕራብ መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት የስራ እንቅስቃሴውን ተዘዋውረው ተመልክዋል።

የምክር ቤቱ አባላት በየአከባቢው እየተከናወኑ ያሉ የልማት ፕሮጀክቶች እንቅስቃሴ ተስፋ ሰጪ ከመሆኑም በላይ ለአካባቢው የቱሪዝም እንቅስቃሴ እንዲያድግና ተጨማሪ ገቢ በመፍጠር ረገድ ትልቅ አስተዋፅኦ ይኖረዋል ነው ያሉት።

በተለይ በቤንች ሸኮ ዞን የተሰሩት እነዚህ የልማት ስራዎች ለአካባቢው ተጨማሪ ውበትን ከመፍጠር ባሻገር ለወጣቶች የሥራ ዕድል ከመፈጠር አኳያ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያበረክታል ነው ያሉት።

በክልሉ የሚገኙ የተፎካካሪ ፓርቲዎች በጋራ ምክር ቤቱ ስር እውቅና አግኝተው በቅንጅት መስራታቸው በአከባቢ ልማትና ዕድገት ላይ የበኩላቸውን ሚና እንዲወጡ ዕድል የፈጠረ መሆኑን ተናግረዋል።

የክልሉ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ምክትል ሰብሳቢ አቶ ግርማ ባሻ እንደተናገሩት ጉብኝቱ በክልሉ እየተሰራ ያለውን የልማት ስራ የጋራ ምክር ቤቱ አባላቶች በተጨባጭ እንዲገነዘብና በቀጣይ ይበልጥ ተቀራርቦ ለመስራት በሚቻልበት መንገድ ላይ ለመወያየት አላማ አድርጎ መዘጋጀቱን ገልጸዋል።

በዞኑ የተሰሩ ግዙፍ የልማት ስራዎች ለአካባቢው የቱሪዝም ዕድገት ለወጣቶች የስራ ዕድል ከመፍጠር ባለፈ ለዞኑ ተጨማሪ ገቢ በመፍጠር ረገድ ትልቅ አስተዋፅኦ ይኖረዋል ብለዋል።

የክልሉ መንግሥት ከተፎካካሪ ፓርቲዎች ጋር ይበልጥ ተቀራርቦ በመስራት የህዝቡን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በርካታ ስራዎች ሲሰራ መቆየቱን ተናግረዋል።

በክልሉ ውስጥ የተረጋጋና ሠላማዊ የፖለቲካ ስነምህዳር እንዲፈጠር ከሁሉም ፓርቲዎች ጋር ተቀራርቦ መስራት ወሳኝ መሆኑንም አቶ ግርማ ገልጸዋል።

የጋራ ምክር ቤቱ አባላት በዞኑ እየተሰሩ ያሉ የተለያዩ የልማት ስራዎችን ተንቀሳቅሰው የመስክ ምልከታ አድርገዋል ሲል የቤንች ሸኮ ቴሌቪዥን ዘግቧል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *