ebtb

Spread the love

የታርጫ ግብርና ምርምር ማዕከል ህንጻ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ርዕሰ መስተዳድር ኢንጅነር ነጋሽ ዋጌሾ (ዶ/ር) በተገኙበት ተመርቀው ለአግልግሎት ክፍት ሆኗል።

የክልሉ አርሶና አርብቶአደሮች ገበያ ተኮር የግብርና ምርቶችን በስፋት በማምረት የኢኮኖሚ ተጠቃሚ እንዲኾኑ ማስቻል እንደሚገባ ዶ/ር ነጋሽ በመድረኩ ተናግረዋል።

የግብርና ምርትና ምርታማነትን በማላቅ በቤተሰብ ደረጃ የምግብ ዋስትና ማረጋገጥ እንደሚገባ የገለጹት ርዕሰ መስተዳድሩ ማዕከሉ ለዚህ መሠረታዊ መዋቅራዊ ሽግግር የሚደግፍ ነው ብለዋል።

በማዕከሉ በምርምርና የዳበሩ የግብርና ውጤቶችን ለአርሶአደሮች በጊዜ ተደራሽ ማድረግ እንደሚገባ ያስገነዘቡት ርዕሰ መስተዳድሩ፥ ከአከባቢው ስነምህዳር ተስማሚ የምርምር ስራዎችን በስፋት ማከናወን ይገባል ብለዋል።

የክልሉ መንግሥት ለግብርና ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ በልዩ ትኩረት እየሰራ መኾኑን የገለጹት ምክትል ርዕሰ መስተዳድርና የግብርና ቢሮ ሀላፊ አቶ ማስረሻ በላቸው፤

በዚህም ከአካባቢው ሥነ-ምህዳር ጋር የተላመዱና ከፍተኛ ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ያላቸውን ዝርፊያ የማባዛት፣ የመስኖ አውታር ዝርጋታ እንዲሁም የአሲዳማ አፈርን ማከም የሚችል የኖራ ማቀነባበሪያ ፋብሪካ ለመገንባት ጥረት እየተደረገ ነው ብለዋል።

ማዕከሉ በአጭር ጊዜ ውስጥ በኮንታ እና ዳውሮ ዞኖች ከ800 በላይ አርሶ አደሮችን ያሳተፈ የኩታገጠም እርሻ ቴክኖሎጂን ማስተዋወቅ መቻሉን የገለጹት የክልሉ የግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር አቶ አማኑኤል አለሙ ናቸዉ።

የዳውሮ በግ ዝርያን በማሻሻል እንዲሁም መሰረታዊ የሰብልና የመኖ መነሻ በዘር አቅርቦት እንዲሁም በተፈጥሮ ሀብትና በእንስሳት ምርምር ዘርፎች ችግር ፈቺ በሆኑ 33 የምርምር ሥራዎች ላይ በጀት መድቦ በስፋት እየተንቀሳቀሰ እንደሚገኝም አስረድተዋል።

ማዕከሉ በሳይንስና ቴክኖሎጂ የታገዘ ምርምር በማካሄድ፣ የአርሶ አደሩን ምርትና ምርታማነት በከፍተኛ ደረጃ በማሳደግ የክልሉንና የሀገሪቱን ብልጽግና ለማረጋገጥ ወሳኝ ሚና እንደሚጫወትም አቶ አማኑኤል ገልጸዋል።

የዳውሮ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ዳዊት ገበየሁ በበኩላቸው ፣ ማዕከሉ በአከባቢው የግብርና ምርትና ምርታማነትን በማላቅ አርሶአደሩን ተጠቃሚ እንደሚያደርግ በመግለጽ፣ ማዕከሉ የዞኑ መንግሥት ቀጣይነት ያለው ድጋፍ እንደማይለይ ተናግረዋል።

በዕድገቱ በዛብህ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *