በክልሉ ባለፉት ዘጠኝ ወራት የተማሪዎች ውጤት ለማሻሻልና የመማር ማስተማር ስራውን ውጤታማ ለማድረግ ዘርፍ ብዙ ተግባራት ተከናውኗል-አቶ አልማው ዘውዴ::

Spread the love

በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልላዊ መንግሥት በ2016 በጀት ዓመት ባለፉት 9 ወራት የተማሪዎች ውጤት መሻሻልና የመማር ማስተማር ስራውን ውጤታማ በማድረግ ረገድ ዘርፍ ብዙ ተግባራት ሲከናወን መቆየቱን በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የማህበራዊ ክላስተር አስተባባርና የትምህርት ቢሮ ኃላፊ አቶ አልማው ዘዉዴ ገልጸዋል።

የ2016 በጀት ዓመት ክልላዊ የትምህርት ልማት ስራዎችን በሚመለከት የክልሉ ትምህርት ቢሮ መግለጫ ሰጥቷል።

በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የማህበራዊ ክላስተር አስተባባርና የትምህርት ቢሮ ኃላፊ አቶ አልማው ዘዉዴ በመግለጫቸው በክልሉ ባለፈው ዓመት በክልላዊ እና በሀገራዊ ፈተናዎች የነበረው የተማሪዎች ውጤት ማሽቆልቆል ለማሻሻል የክልሉ ትምህርት ቢሮ በየደረጃው ባሉት መዋቅሮችና አካላት ጋር በትኩረት እየሰራ ስለመሆኑን ተናግረዋል።

በክልሉ በሚገኙት 1ሺ 114 አንደኛና፣ በ167 2ኛ ደረጃ ት/ቤቶች ውስጥ ለሚገኙ ተማሪዎች ሀገራዊና ክልላዊ ፈተናዎች ላይ ያለፈውን ውጤት በሚያካክስ መልኩ አመርቂ ውጤት መመዝገብ እንዲችሉ ትኩረት ተሰጥቶ የትምህርት ልማት ሥራ እየተሰራ መሆኑን ነው አቶ አልማው ዘውዴ ገልፀዋል፡፡

የ8ኛ ክፍል ክልላዊ ፈተና ሰኔ ከ4 እና 5/2016 እንዲሁም የ12ኛ ክፍል ሀገራዊ ፈተና ሰኔ 15-25 /2016 ዓ.ም ባሉት ቀናት የሚሰጥ መሆኑን የጠቆሙት የቢሮ ኃላፊው የዘንድሮ የ8ኛ ክፍል ተፈታኝ ተማሪዎችም በቂ ቅድመ ዝግጅት እንዲያደርጉና ከመምህራኞችም የማጠናከሪያና የድጋፍ ትምህርቶች እየተሰጠላቸው ነው ብለዋል ።

የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና በሚመለከት የካፋ እና የኮንታ ዞን ተማሪዎች በቦንጋ ዩኒቨርስቲ፣የዳውሮ ዞን በወላይታ ሶዶ ዩንኗኒቨርስቲ በታርጫ ካምፓስ ፣የምዕራብ ኦሞ ዞንና የቤንካምስፓኮ ዞን የሚዛን ዩኒቨርስቲ በሚዛን ካምፓስ እንዲሁም የሸካ ዞን ተማሪዎች በሚዛን ዩኒቨርስቲ በቴፒ ካምፓስ እንደሚወስዱም ተገልጿል።

በዚህም በክልላችን ያሉ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የቦንጋ ዩኒቨርስቲ እና የሚዛን ቴፒ ዪኒቨርስቲ ተማሪዎችን የመደገፍና የማብቃት ስራዎች በስፋት እያከናወኑ እንደሚገኝም ኃላፊው ጠቁመዋል።

የትምህርት ቤቶችን ደረጃ ለማሻሻል እንደሀገር ልዩ ትኩረት ተደርጎ የትምህርት ለትውልድ ንቅናቄ በጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አህመድ አነሳሺነት የተጀመረውን ከማሳካት አንጻር ከሐምሌ 2015 ዓ/ም ጀምሮ እየተከናወነ እንደሚገኝ አቶ አልማዉ ገልጸዉ በዚህም የሕብረተሰብ ተሳትፎን ጨምሮ ተስፋ ሰጪ ውጤቶች እየተመዘገቡ ናቸው ሲሉም ገልጸዋል።

ከአዲሱ የትምህርት ፍኖታ ካርታ ትግበራ ጋር ተያይዞ የተከሰተውን የመፅሐፍ ጥምርታ ክፍተት ለማስተካከል በየደረጃው ባሉ መዋቅሮች ሰፊ ርብርብ ተደርጎ መሰራቱን ገልጸው፥ በህብረተሰብ ተሳትፎ ሆነ በመንግስት በኩል ልዩ ትኩረት ተደርጓል ብለዋል፡፡

በክልሉ አዳሪ ትምህርት ቤቶችን በመገንባት እና አስፈላጊውን ግብዓት በማሟላት የተማሪዎች ውጤት እንዲሻሻል መጠነ ሰፊ ጥረቶች እየተደረጉ መሆናቸውን ጠቁመው ይህንን ከማስቀጠል አኳያ ዞኖች የድርሻቸውን እንዲወጡም መክረዋል፡፡

በአንዳንድ ዞኖች ከበጀት እጥረት ጋር ተያይዞ የተከሰተውን ችግር ክልሉ ልዩ ድጋፍ በማድረግ በሚቀጥለው የትምህርት ዘመን እልባት እንዲያገኙ እየሰራ መሆኑን አቶ አልማው ገልጸዋል ፡፡

ለትምህርት ጥራትና ለተማሪዎች ውጤት መሻሻል የመምህራንና የትምህርት ባለድርሻዎች ሚና ወሳኝ ጉዳይ መሆኑን የገለጹት የቢሮ ኃላፊው በቦንጋ ትምህርት ኮሌጅ ከሰርትፊኬት ጀምሮ እስከ መጀመሪያ ድግሪ ድረስ ከ700 በላይ መምህራን እያሰለጠኑ መሆናቸውን አስረድተዋል ፡፡

ት/ቤቶች የውስጥ ገቢ አቅማቸውን ማሳደግ እንዲችሉ የሐብት ኦዲትና ምርመራ ሥራ ደረጃውን በጠበቀ ሁኔታ እየተከናወነ መሆኑን አቶ አልማው ተናግረዋል ፡፡

የተማሪዎችን ምገባ ሥርዓት በማጠናከርና በተለያዩ ምክንያቶች ከትምህርት ገበታ የሚለዩትን ተማሪዎች ከመደገፍ አንጻር ሚናው የላቀ መሆኑን የገለጹት አቶ አልማው፥ የተጀመረው እንቅስቃሴ ተጠናክሮና የትምህራት ስብራት ታደሶ በመጪው ዘመን የተሻለ ውጤት ለማየት ሁሉም በተሰማራበት የትውልድ አደራውን ሊወጣ ይገባል በማለት አሳስበዋል፡፡

በፍቅር ከበደ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *