





በክልሉ ቤንች ሸኮ ዞን ጉራፈርዳ ወረዳ በአንዲት ሴት ሞዴል አርሶአደር እየተከናወነ የሚገኝ የወተት ላሞች እርባታን በአቶ ማስረሻ በላቸዉ የተመራ ልዑክ ጎብኝተዋል።
ወ/ሮ ሞሚና ጀማል በወረዳው ኩጃ ቀበሌ አዲስአለም መንደር በቤተሰብ ይዞታ ላይ የወተት ላሞችን እያረቡ እንደሚገኙ ተናግረዋል።
በአረብ ሀገር ለስራ በመሄድ ሰርተው ያገኙትን ሀብት የወተት ላሞችን በመግዛት እርባታ መጀመራቸውን ወ/ሮ ሞሚና ተናግረዋል ።
አስራ አንድ የተሻሻሉ ዝርያ ያሏቸውን ላሞች በመግዛት ስራ በጀመሩ ስድስት ወራት ውስጥ 3 ጥጆችን በማግኘት የሰራቸውን አስራ አራት አድርሰዋል ።
ከአንድ ላም በቀን ዝቅተኛው 8 ሊትርና ከፍተኛው 46 ሊትር ወተት እንደሚያገኙም ወ/ሮ ሞሚና ተናግረዋል ።
አሁን ላይ ከሚታለቡ የወተት ላሞች በቀን 130 ሊትር ወተት በማግኘት ለአካባቢው ነዋሪዎች የወተት አቅርቦት ዕጥረትን በመቀነስ የበኩላቸውን እየተወጡ እንደሚገኙም ተናግረዋል ።
ወ/ሮ ሞሚና በዚሁ ስራቸው ለ25 ሰዎች የስራ ዕድል መፍጠር መቻላቸውንም ለልዑኩ አስረድተዋል ።
በቀጣይም ስራቸውን አስፋፍተው በዶሮ እርባታ፣በበግ ማሞከትና በንብ ማነብ ስራ ለመሰማራት ዕቅድ እንዳላቸውም አስረድተዋል።
ለዚህ ስራ ውጤታማ መሆን የባለሙያዎች ያልተቋረጠ ድጋፍ መሆኑንም አብራርተዋል ።
አሁን የሌማት ትሩፋት ስራውን የሚሰሩበት ይዞታ የቤተሰብ በመሆኑ ስራቸውን ለማስፋፋት ተጨማሪ መሬት እንደሚያስፈልጋቸው ጠይቀዋል።
ከሀገር ውጭ ያሉና ለመሄድም ፍላጎት ያሏቸው ሴት ኢትዮጵያዊያንን በሀገር ሰርቶ መበልጸግ እንደሚቻል የኔ ውጤት ማሳያ ነው ሲሉም ተናግረዋል ።
በታጠቅ አበበ
