





የዞኑ ገበያ ልማት እና እንቨስትመንት መምሪያ በዞኑ ካሉ ባለሀብቶች ጋር የእንቨስትመንት ምክክር ፎረም አካሂዷል።
የመምሪያው ሀላፊ ወ/ሮ ታሪኳ ታከለ በዞኑ ወደ 3 መቶ 29 ኢንቨስተሮች መኖራቸውን በመጠቆም በየዘርፉ የተሰማሩ ባለሀብቶች በትኩረት መስራት ከቻሉ ውጤታማ መሆን ይችላሉ ብለዋል።
የእንቨስትመንት ስርጭቱ በሁሉም ወረዳዎች የተዳረሰ ሲሆን የሚታዩ ክፍተቶችን በማረም ከራስ ባሻገር ለህብረተሰቡ ተጠቃሚነትም መስራት እንዳለባቸው አሳስበዋል።
የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ አቶ እንዳሻው ከበደ ባለሀብቶች ያለ ተግዳሮት ተንቀሳቅሶ መስራት እንዲችል የተለያዩ ስራዎች እየተከናወኑ መሆናቸውን ጠቁመዋል ።
ይሁንና በአንዳንድ ባለሀብቶች ላይ የሚታዩ መሬት ከወሰዱ በኋላ በአግባቡ ያለማልማት ችግር፣ በገቡት ዉል መሠረት ወደ ስራ ያለመግባት፣ የተሻሻሉ አሠራሮችን ያለመጠቀም እና ግብርን በወቅቱና በተገቢው ያለመክፈል ችግሮች ልታረሙ ይገባቸዋል ብለዋል።
ህጉን ተከትለው በማይሠሩ ባለሀብቶች ላይ መሬታቸውን ከመውሰድ ጀምሮ የተለያዩ ህጋዊ እርምጃ እንደምወሰድባቸውም ገልጸዋል ።
የዉይይት ሰነዱን ያቀረቡት የመምሪያው ምክትል ሀላፊና የእንቨስትመንት ዘርፍ ሀላፊ አቶ ሀብታሙ ገ/ስላሴ የግል ባለሀብቱ የተጣለበትን የገቢ ግብር በአግባቡና በጊዜ በመክፈል ለአካባቢው ልማት አሻራውን ከማሳረፍ ባለፈ ሀገራዊ ግዴታውን ሊወጣ ይገባል ብለዋል።
በመድረኩ ከተሳተፉት ባለሀብቶች መካከል የሙለጌ ካፋ ቢጣ ቡና ልማት ስራ አስከያጅ አቶ ሻረው ገብሬ እና ብርሃኑ ሀይሌ ቡና እርሻ ድርጅት ስራ አስኪያጅ አቶ ብርሃኑ ሀይሌ በአካባቢያቸው የተለያዩ መሠረተ ልማቶችን በመስራት ማህበራዊ ግደታቸውን እየተወጡ መሆናቸውን ተናግረዋል።
የተለያዩ የመሠረተ ልማት ጥያቄዎች፣ የፀጥታ ችግርና የባንክ ብድር አለመመቻቸት ችግር እንዲፈታላቸውም ጠይቀዋል ።
ከተሳታፊዎች ለተነሱ ጥያቄዎች ከባለድርሻ አካላት ምላሽና ማብራሪያ ተሰጥቷል ።
በመድረኩ የዞኑ ከፍተኛ አመራሮችን ጨምሮ የሁሉም ወረዳ አስተዳዳሪዎች ፣ የተለያዩ ባለድርሻ አካላት እና የግል ባለሀብቶች ተገኝተዋል ሲል ቦንጋ ኤፍኤም 97.4 ዘግቧል።
