በኦሊምፒክ ጨዋታዎች ለተሳተፈው የኢትዮጵያ ልዑካን ቡድን ብሔራዊ የጀግና አቀባበል ይደረግለታል – የባህልና ስፖርት ሚኒስቴር

Spread the love

በፓሪስ በተካሄደው 33ኛው የኦሊምፒክ ጨዋታዎች ለተሳተፈው የኢትዮጵያ ልዑካን ቡድን ብሔራዊ የጀግና አቀባበል እንደሚደረግለት የባህልና ስፖርት ሚኒስቴር አስታወቀ።

አትሌቶች በውድድሩ የሚገባውን ተጋድሎ መፈጸማቸውን ገልጿል።

ሚኒስቴሩ የኢትዮጵያን የኦሊምፒክ ተሳትፎ በማስመልከት መግለጫ አውጥቷል።

ኢትዮጵያ እ.አ.አ በ1956 በሜልቦርን በተካሄደው 16ኛው የኦሊምፒክ ጨዋታዎች አንስቶ በአጠቃላይ 15 ጊዜ ተሳትፎ ማድረጓን ገልጿል።

ከሜልቦርኑ በስተቀር ከኦሎምፒክ በ14ቱ የተሳትፎ መድረኮች ካለ ሜዳሊያ ተመልሳ አታውቅም ብሏል።

በአጠቃላይ ኢትዮጵያ በመድረኩ 24 ወርቅ፣ 15 ብር እና 23 ነሐስ በድምሩ 62 ሜዳሊዎችን በማግኘት በዓለም መድረክ ደማቅ ታሪክ ካላቸው ሀገሮች ተርታ መሰለፏን አመልክቷል።

መንግስት በኢትዮጵያ የኦሊምፒክ ፍልስፍና እንቅስቃሴ ሰፊ ሕዝባዊ መሰረት እንዲኖረው እየሰራ እንደሚገኝ ነው ሚኒስቴሩ ያስታወቀው።

በኦሎምፒክ አገርን የሚወክሉ አትሌቶችን በመመልመል፣ በማሰልጠንና በማወዳደር በኦሎምፒክ አደባባይ ውጤት በማስመዝገብ የኢትዮጵያን መልካም ገፅታ ለመገንባት አስፈላጊ ጥረት በየጊዜው እንደሚከናወን ገልጿል።

ኢትዮጵያ በ33ኛው የኦሊምፒክ ጨዋታዎች 1 የወርቅና 3 የብር በድምሩ 4 ሜዳሊያዎችን በማግኘት 47ኛ ደረጃን ይዛ አጠናቃለች።

አትሌቶቹ በተሳተፉበት ውድድር ሁሉ ለሀገር የሚገባውን ተጋድሎ ፈጽመዋል፣ ለዚህም ሀገራዊ ምስጋናና ክብር ይገባቸዋል ነው ያለው ሚኒስቴሩ።

በኦሊምፒኩ ውጤት ላስመዘገቡና ለተሳተፉ የኢትዮጵያ ልዑካን ቡድን አባላት ነገ ማለዳ በቦሌ ዓለም አቀፍ አየር መንገድ የብሔራዊ ጀግና አቀባበል እንደሚደረግላቸው ጠቁሟል።

በዕለቱ ለልዑካን ቡድኑ በብሔራዊ መንግስት የእውቅናና የሽልማት መርሐ ግብር እንደሚካሄድ ኢዜአ ከባህልና ስፖርት ሚኒስቴር ያገኘው መረጃ ያመለክታል ሲል ኢዜአ ዘግቧል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *