
የሸካ ተፈጥሮ ደን ህብረተሰቡ በሀገር በቀል ዕውቀቱ በባህላዊ መንገድ ጠብቆ ያቆየው የማህበረሰቡ የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ እሴት ውጤት ነው። ደኑ እስከ አሁን የብዝሃ ህይወት ስብጥሩን ሳይለቅ ከትውልድ ትውልድ እየተሸጋገረ መምጣቱ ህብረተሰቡ ለተፈጥሮ ሀብት ያለውን ተቆርቋሪነት የሚያመላክት ነው። ሸካዎች የተፈጥሮ ደኑ የምግብ፣ የመድኃኒት፣ የመጠለያና የመዝናኛ ምንጭ እና መሠረትም ነው ብለው ያምናሉ።
በተለያዩ የተፈጥሮ ፀጋዎች የታደለው የሸካ ምድር ካለው 238 ሺሕ 750 ሄክታር የቆዳ ስፋት ከ131 ሺሕ 639 ሄክታር በላይ የተሸፈነው በጥብቅ የተፈጥሮ ደን መሆኑን መረጃዎች ያመላክታል። ከአጠቃላይ ቆዳ ስፋቱ 55 በመቶው በጥብቅ የተፈጥሮ ደን እንደተሸፈነ የሚነገርለት የሸካ ደን ወደ 28 ሺሕ ሄክታር የሚጠጋ የቀርቀሃ ደን ክምችት ያለበትም ነው፡፡
ደኑ በውስጡ ዝግባን ጨምሮ ቀረሮ፣ ዋርካ፣ ጎንጂ፣ ጥቁር እንጨት እና ሌሎች ግዙፍ ሀገር በቀል የዛፍ ዝሪያዎች የሚገኙበት ሲሆን ከ650 በላይ የብዝሃ ህይወት ስብጥር ይገኝበታል፡፡
በአረንጓዴ ውበቱ ቀልብን የሚማርከው ጥቅጥቅ የተፈጥሮ ደኑ በውስጡ ከ300 በላይ የዛፍ ዝሪያዎች፣ 50 አጥቢ የዱር እንስሳት፣ 2 መቶ የሚሆኑ የወፍ እንዲሁም 20 የተሳቢ እንስሳት ዝርያዎችንም አቅፎ ይዟል።
አከባቢው ዓመቱን በሙሉ ዝናብ የማይታጣና በገፀ ምድርና በከርሰ ምድር ውሃ ክምችት የታደለም ነው። የባሮ፣ በቆ፣ ጋሃማዎ፣ ገማድሮ፣ መነሺ ወንዝ እና ሌሎችን ጨምሮ ከ32 በላይ የሚሆኑ ዓመቱን በሙሉ የሚፈሱ ትልልቅ ወንዞች ምንጫቸውና መነሻቸው ከዚሁ ከጥብቁ የሸካ የተፈጥሮ ደን ነው።
የሸካ ዞን የተፈጥሮ እና የሰው ሠራሽ የመስህብ ሥፍራዎች የሚገኙበት ድንቅ የቱርዝም መዳረሻዎች ያሉበት ነው። ከ46 በላይ ፏፏቴዎች፣ ከ20 በላይ ዋሻዎች እንዲሁም በልዩ አፈጣጠሩ በደጋመው ተራራ ላይ በቀርቀሃ ደን የተከበበውን የጋንዲዎችን ሀይቅ ጨምሮ ሦስት የደጋ ሀይቆች በዞኑ ይገኛሉ፡፡ ወደ 51 የሚጠጉ ሆራዎች በደኑ ውስጥ እንደሚገኙም መረጃዎች ያሳያሉ።
በሀገር በቀልና ዕድሜ ጠገብ የዛፍ ዝሪያዎች የተሸፈነው ይህ አረንጓዴው ምድር የጫካ ቡናን ጨምሮ፣ ማር፣ ኮረሪማ፣ ጥምዝ፣ ሔል፣ ቁንዶበርበሬ፣ ዝንጅብል፣ እርድ እንዲሁም እንሰትና የተለያዩ ፍራፍሬዎች የተፈጥሮ ደኑን ሳይረብሹ ይመረታሉ፡፡
የተፈጥሮ ደኑ በተባበሩት መንግስታት የሳይንስ፣ ትምህርትና ባህል ድርጅት ዩኔስኮ እ.ኤ.አ ሐምሌ 2012 መመዝገቡ ይታወሳል።
አዲስ ዋልታ
