የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የቀድሞ ምሩቃን ቀን ፕሬዚዳንት ታዬ አጽቀሥላሴ በተገኙበት እየተከበረ ነው

Spread the love

የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የቀድሞ ምሩቃን ቀን የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ታዬ አጽቀሥላሴ በተገኙበት በስድስት ኪሎ ካምፓስ እየተከበረ ነው።

በመድረኩ ላይ ንግግር ያደረጉት የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተጠባባቂ ፕሬዚዳንት ሳሙኤል ክፍሌ (ዶ/ር)፥ ዩኒቨርሲቲው ላለፉት 74 ዓመታት በርካታ ምሁራንን ማፍራቱን ገልፀዋል።

ዩኒቨርሲቲው በተለያዩ ዘርፎች የተሰማሩ ምሁራንን ከማፍራትም ባለፈ በጥናትና ምርምር ዘርፍ ለሀገር የላቀ አስተዋጽኦ ማበርከቱንና አሁንም ይህንኑ አጠናክሮ መቀጠሉን ገልፀዋል።

የዕውቀት ማዕከልነቱን ለማስቀጠልም ራስ ገዝ ሆኖ በአዲስ መልክ በመደራጀት ዘመን ተሻጋሪ የትምህርት፣ ጥናትና ምርምር ስራዎችን በማከናወን ላይ ይገኛል ነው ያሉት።

ቀኑ መከበሩ የዩኒቨርሲቲው የቀድሞ ተማሪዎች ከያሉበት ተሰባስበው የተጠናከረ ትስስር ለመፍጠርና የተቋሙን አቅም ለማጎልበት መልካም አጋጣሚ ስለመሆኑም አንስተዋል።

በመድረኩ ልዩ ልዩ የቀድሞ ምሩቃንን ትዝታ የሚያስታውሱ የኪነ-ጥበብና የመዝናኛ ትዕይንቶች መቅረባቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

በመርሐ ግብሩ ላይ ከፕሬዚዳንት ታዬ አጽቀሥላሴ በተጨማሪ ሚኒስትሮች፣ በዩኒቨርሲቲው የተማሩ ምሁራን እንዲሁም ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።

በዩኒቨርሲቲው የተማሩና አሁን ላይ በተለያዩ የስራ ሃላፊነት ላይ የሚገኙ ምሁራንና ታዋቂ የኪነ-ጥበብ ሰዎችም በሥነሥርዓቱ ላይ ታድመዋል ሲል ኢቢሲ ዘግቧል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *