ሕብረቱ የመፈጸም አቅሙንና ውጤታማነቱን ለማሳደግ የሰው ኃይል ብቃትና ተወዳዳሪነት ላይ በትኩረት ሊሰራ ይገባል፦ አምባሳደር ምስጋኑ አርጋ

Spread the love

የአፍሪካ ሕብረት የመፈጸም አቅሙንና ውጤታማነቱን ለማሳደግ የሰው ኃይል ብቃትና ተወዳዳሪነት ላይ በትኩረት መስራት እንደሚገባው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ምስጋኑ አርጋ ገለጹ።

23ኛው የአፍሪካ ሕብረት የስራ አስፈጻሚ ምክር ቤት አስቸኳይ ስብሰባ በበይነ መረብ ተካሂዷል።

በውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ምስጋኑ አርጋ የተመራ የኢትዮጵያ ልዑክ በስብሰባው ተሳትፏል።

ስብሰባው የተደረገው እ.አ.አ በጁላይ 2024 በጋና አክራ በተካሄደው 45ኛው የምክር ቤቱ መደበኛ ስብሰባ የተላለፉ ውሳኔዎችን መሰረት በማድረግ ነው።

ውይይቱ የአፍሪካ ሕብረት የክህሎት ግምገማ እና የብቃት ኦዲት ሂደት (SACA)፣ ከኦዲት ጋር የተገናኙ ጉዳዮች እና ሕብረቱ የቡድን 20(G-20) ቋሚ አባል መሆኑን ተከትሎ አፍሪካ በስብስቡ ቅድሚያ የምትሰጣቸው ስትራቴጂካዊ ጉዳዮች ላይ ያተኮረ መሆኑ ተገልጿል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ምስጋኑ አርጋ የአፍሪካ ሕብረት የክህሎት ግምገማና የብቃት ኦዲት ሂደት(SACA)ን አስመልክቶ ከዚህ ቀደም የተላለፉ የፖለሲ ውሳኔዎችን በአግባቡ መተግበር እንደሚገባ ገልጸዋል።

“SACA” የአፍሪካ ሕብረትን የሰው ኃይል ብቃት እና ተወዳዳሪነት የሚያሻሽል በመሆኑ የኮሚሽኑን የመፈጸም አቅምና ውጤታማነት ለማሳደግ የማዕቀፉን ትግበራ ማፋጠን እንደሚገባ አመልክተዋል።

በስብሰባው የአፍሪካ ሕብረት ኮሚሽን ሕብረቱ እ.አ.አ በሕዳር ወር 2024 በብራዚል ሪዮ ዴጄኔሮ በተካሄደው የቡድን 20(G20) የመሪዎች ስብሰባ ላይ የነበረውን ተሳትፎ አስመልክቶ ያቀረበውን ሪፖርት ተገምግሟል።

የስራ አስፈጻሚ ምክር ቤቱ ሪፖርቱን ያጸደቀ ሲሆን የአፍሪካ ሕብረት በዓለም አቀፍ መድረክ የአፍሪካን ፍላጎቶች ስኬታማ በሆነ መልኩ ማንጸባረቁን አድንቋል።

የውይይቱ ተሳታፊዎች የአፍሪካን ድምጽ በዓለም አቀፍ መድረኮች ይበልጥ አጉልቶ ለማሰማት ዘላቂ ጥረት ማድረግ እንደሚገባም ገልጸዋል።

ተሳታፊዎቹ ደቡብ አፍሪካ የቡድን 20 ፕሬዝዳንት በመሆኗ የደስታ መግለጫ መልዕክታቸውን ያስተላለፉ ሲሆን ሀገሪቱ በቆይታዋ ከአፍሪካ ሕብረት ጋር በመሆን የአፍሪካን የቅድሚያ ትኩረቶች ለማንጸባረቅ መስራት እንደሚገባትም አሳስበዋል።

የስራ አስፈጻሚ ምክር ቤቱ በአስቸኳይ ስብሰባው የተለያዩ የውሳኔ ሀሳቦችን አፅድቋል።

ምክር ቤቱ የአፍሪካ ሕብረትን ውስጣዊ አቅም እና ዓለም አቀፍ ተጽእኖ ፈጣሪነትን ለማጠናከር በቁርጠኝነት እንደሚሰራ መግለጹን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያመለክታል ሲል ኢዜአ ዘግቧል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *