በሸኮ ከተማ ከ2 ነጥብ 8 ሚሊየን ብር በላይ በጀት የከተማውን ህብረተሰብ ተጠቃሚ የሚያደረጉ ዘርፈ ብዙ ተግባራት እየተከናወኑ ነው – የከተማው አስተዳደር

Spread the love

በሸኮ ከተማ ከ2 ነጥብ 8 ሚሊየን ብር በላይ በጀት የከተማውን ህብረተሰብ ተጠቃሚ የሚያደረጉ ዘርፈ ብዙ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑን የከተማው አስተዳደር አስታወቀ።

የከተማ ነዋሪዎችን የልማቱ ተጠቃሚ ለማደረግ በሚደረገው ጥረት ልማቱን ለማገዝ የተጀመረው ርብርብ ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባም ተገልጿል።

በቤንች ሸኮ ዞን በሸኮ ወረዳ የሚገኘው የሸኮ ከተማ አስተዳደር በተያዘው በጀት ዓመት በወርሃ ነሐሴ 3/2016 ዓመተ ምህረት ከተመሠረተበት ጊዜ ጀምሮ የከተማውን ነዋሪዎችና ህብረተሰቡን ተጠቃሚ የሚያደረጉ ዘርፈ ብዙ ልማቶችን በማከናወን አጠናክሮ መቀጠሉ ተገልጿል።

የ350 ሚሊየን ፕሮጀክት አካል የሆነው የሸኮ ከተማ አስተዳደር ከሸኮ ወረዳ ጋር በጋራ በመሆን በበጀት ዓመቱ 112 ሚሊየን ብር በላይ በመሰበሰብ በከተማም ሆነ በገጠሩ ወሳኝ የሆኑ ተግባራትን ለማከናወን ታቅዶ እየተሰራ እንደሚገኝ የሸኮ ከተማ አስተዳደር ዋና ከንቲባ አቶ ታምራት ምናሴ ተናግረዋል።

በዚህም እስካሁን ባለው 2 ሚሊየን ብር ተሰብስቦ የከተማውን ህዝብ ተጠቃሚ የሚያደረጉ 1 ኪሎ ሜትር የመንገድ ከፈታ፣ 75 በመቶ የሚሆን የስታድየም ግንባታ ቦታ ቆረጣና የገበያ ቦታ በማስመንጠር 2.8 ሚሊየን ብር የንብረት ካሳ ክፍያ ተፈፅሞ ከይገባኛል ነፃ የማደረግ ተግባራት ከማዘጋጃ ቤት ጋር እየተከናወኑ መሆኑን ከንቲባው ገልፀዋል።

ባለፈው 2016 በጀት ዓመት ከ350 ሚሊየን ፕሮጀክት 33 ኪሎ ሜትር መንገድ ጠረጋ የተከናወነ ሲሆን በዘንድሮ ዓመትም 20 ኪ.ሜ በማስጠረግና የአምናውን መንገድ ጠጠር የማልበስ ስራ እንደሚሰራም አቶ ታምራት ተናግረዋል።

ከተያዘው የሸኮ ከተማ መልሶ የማልማት ሥራ የኢንቨስትመንት ቦታ ከወሰዱ 5 ሰዎች 4ቱ ወደ ተግባር የገቡ ሲሆን ቀሪውን ገምግሞ ወደ ልማት ከማስገባትም ባለፈ ተጨማሪ ቦታዎችን ለይቶ ለባለሀብት ለማስተላለፍ ጥረት እየተደረገ መሆኑን ከንቲባው አብራርተዋል።

ከተማ አስተዳደሩ በማህበራዊ ዘርፍም የደሃ ደሃ ለሆኑ 7 ግለሰቦች ቤት ሰርቶ ለመስጠት አቅዶ 4 ቤቶች ተሰርቶ መጠናቀቁን ቀሪውን ለማሳካት ርብርብ እያደረገ ከመሆኑም ባለፈ ለ19 ተማሪዎች የትምህርት ግብዓት ተሟልቶ እንዲማሩ፣ ለ250 የድሃ ደሃዎች ደግሞ የማዕድ ማጋራት ተግባራትን አከናውኗል።

በትምህርት ዘርፍም በክልሉ ርዕሰ መስተዳደር ኢኒሼቲቭ የቅድመ አንደኛ ደረጃ ት/ቤት ደረጃን ከፍ ማደረግ እንዲሁም በ2009 ዓ.ም ተጀምሮ ለ7 ዓመት የቆየውን የሸኮ ከፍተኛ 2ኛ ደረጃ ት/ቤት ወደ 5 ክፍሎችን ከ550 ሺህ ብር በላይ በጀት በመመደብ የማጠናቀቅ ሥራ መከናወኑን ዋና ከንቲባው ተናግረዋል።

ከ20 በላይ ኮምፒውተሮችን ለትምህርት ቤቱ ለመሟላት 240 ሺህ ብር ከንቲባ ጽህፈት ቤት መመደቡን አቶ ታምራት አውስተው የመፅሐፍት ዕጥረትን ለመፍታት ለአንድ ተማሪ አንድ መፅሐፍ በሚለው መሪ ቃል ከ50 ሺህ ብር በላይ ድጋፍ ተደርጓል ብለዋል።

በአሁን ሰዓት በሸኮ አካባቢው እየመጣ ባለው ለውጥ ከፍተኛውን ሚና ለተወጡ የሸኮና አካባቢው ምሁራን ጥናትና ምርምር ማህበር ጽህፈት ቤት ግንባታ የሚውል 1 ሺህ ካሬ ሜትር ቦታ ማሰረከቡን ከንቲባው ገልጸዋል።

በከተማ አስተዳደሩ አንድ 2ኛ እና 4 የመጀመሪያ ደረጃ ት/ቤቶች 3ሺህ 874 ተማሪዎች እንደሚገኙና የትምህርት ጥራትን ለማስጠበቅ እየተሰራ ነው ያሉት በከተማ አስተዳደሩ የማህበራዊ ዘርፍ አስተባባሪ አቶ ከድር ይማም የሸኮ ከፍተኛ 2ኛ ደረጃ ት/ቤትን ለማጠናከር ትምህርት ይመለከተኛል የሚሉ ድጋፍ እያደረጉ ነው ብለዋል።

በከተማው የህብረተሰቡን የልማት ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ በሚደረገው ጥረት ለወጣቶች መዝናኛ የሚሆን 3 ሄክታር መሬት ስታድየም በማዘጋጀትና በማሳረስ የሸኮ ብሄረሰብ ዘመን መለወጫ የ”ቲካሻ ቤንጊ” በዓል ማክበሪያና የገበያ ቦታዎች ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን የከተማው ማዘጋጃ ቤት ጽፈት ቤት ኃላፊ አቶ ማቴዎስ እንግሊዝ ተናግረዋል።

ከተማው በብዛት በቡና የተሸፈነ አካባቢ በመሆኑ ህብረተሰቡ እንዳይጎዳ ገንዘብ በማሰባሰብ 3 ሚሊየን የንብረት ካሳ ከመከፈሉም ባሻገር ውሃ መብራት ለከተማው ወሳኝ በመሆኑ የማስፋፋት ስራ እየተሰራ መሆኑን ኃላፊው አውስተው የውስጥ ለውስጥ መንገድን በመጠበቅ ረገድ ሁሉም ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ ጥሪ ማቅረባቸዉን ደሬቴድ ሚዛን ቅርንጫፍ ዘግቧል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *