




የኢትዮጵያ ግብርና ስራዎች ኮርፖሬሽን የኮካ እርሻ ማቋቋሚያ የመሬት ልማት ማስጀመሪያ የአጋሮች የውይይት መድረክ በቱም ከተማ እያካሄደ ነው።
የኢትዮጵያ ግብርና ስራዎች ኮርፖሬሽን ለኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ ተጠሪ ከሆኑ ተቋማት አንዱ መሆኑንና ግብርናን ለማዘመን ተልዕኮ የተሰጠውና በአምስት አንጋፋ የልማት ድርጅቶች ውህድ የተቋቋመ የመንግስት የልማት ድርጅት ነው ።
ኮርፖሬሽኑ የህዝብ ተቋም እንደመሆኑ መጠን ግብርናን በማዘመን በሀገር ደረጃ ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ የምግብ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ የድርሻውን ለማበርከት በስፋት እየተንቀሳቀሰ እንደሚገኝ የኮርፖሬሽኑ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ክፍሌ ወልደማርያም ተናግረዋል ።
ኮርፖሬሽኑ በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ከ2013 ዓ/ም ጀምሮ ወደ ስራ ለመግባት በክልሉ ያለውን እምቅ የተፈጥሮ ሀብትና ለስራ ታታሪ የሆነ የልማት ጥያቄን ያነገበ እና ለሰላም ዋጋ የሚሰጥ ህዝብና የፖለቲካ አመራር የሚገኝበት በመሆኑ ክልሉን መምረጡን ተናግረዋል።
ኮርፖሬሽኑ በክልሉ የታማሻሎ የምርጥ ዘር ማባዣ እርሻ ልማት ፣ በቅርቡ የሚመረቀው የቦንጋ የተቀናጀ የግብርና ግብኣትና የሜካናይዜሽን አገልግሎት ማዕከል ቀጥሎ የኮካ ቀበሌ የእርሻ ማቋቋሚያ የመሬት ልማት የሰብል ዘሮችን ለማባዛት እና ለውጭ ገበያ የሚላኩ ምርቶችን በስፋት ለማምረት በክልሉ ሶስተኛው መዳረሻ መሆኑን አቶ ክፍሌ ተናግረዋል ።
የኢትዮጵያ ግብርና ስራዎች ኮርፖሬሽን የአርሶና አርብቶ አደሩን ከእጅ ወደ አፍ የሆነውን ኋለቀር የግብርና ዘይቤ በመቀየርና ቴክኖሎጂን በማስረጽ ለአካባቢው ነዋሪዎች በቅርበት ሆኖ ያገለግላል ሲሉም አቶ ክፍሌ ተናግረዋል ።
የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ብሔረሰቦች ምክርቤት ዋና አፈጉባኤ የተከበሩ አቶ መቱ አኩ በበኩላቸው ልማቱ የአርብቶና አርሶ አደሩን ህይወት የሚቀይርና ግብርናን የሚያዘምን ነው ሲሉ ተናግረዋል ።
የኢትዮጵያ ግብርና ስራዎች ኮርፖሬሽን ውጤታማ እንዲሆንም የአካባቢው ነዋሪዎች በቅንጅትና በትብብር መስራት ይጠበቅባቸዋል ብለዋል።
በክልሉ በምዕራብ ኦሞ ዞን በኮካ ቀበሌ የመጣውን የልማት ዕድል ሳንጠቀም አልፎን ትውልድ እንዳይወቅሰን በመተባበርና በመደማመጥ ወደ ስራ መግባት ይኖርብናል ሲሉም አቶ መቱ ተናግረዋል ።
የኢትዮጵያ ግብርና ስራዎች ኮርፖሬሽን ገጽታና እያከናወነ ያለውን ስራዎች የተመለከተ ሰነድ ቀርቦ በተሳታፊዎች ውይይት እየተደረገበት ነው።
በታጠቅ አበበ
