ቆይታከእኛጋር!

Spread the love

“ከተማን ለማምረት የከተማ ፕላን አስገዳጅ ነው”፡- የክልሉ ከተሞች ፕላን ኢንስቲትዩት


የዚህ ወር “ቆይታ ከእኛ ጋር” እንግዳችን ፕሮግራም
የዛሬው ቆይታ ከእኛ ጋር ተጋባዥ እንግዳችን አቶ ፀጋዬ ሀይሌ ይባላሉ። በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ከተሞ ፕላን ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ናቸው። የክልሉ የከተማ ፕላን ኢንሰስቲትዩት የስራ እንቅስቃሴ፣ የከተሞች አደረጃጀት እንዲሁም የፕላን ዝግጅትና ትግባራ ሂደትን በሚመለከት ከክልሉ የመንግስት ኮሙኒኬሽን ጋር ቆይታ አድርገዋል።
መልካም ንባብ!
መ/ኮ፦ የክልሉ የከተማ ፕላን ኢንስቲትዩት አጠቃላይ የስራ እንቅስቃሴን ብገልጹልን?


አቶ ፀጋዬ ኃይሌ፦ የክልሉ ፕላን ኢንስቲትዩት በዕቅድ ላይ የተመሰረተ የከተሞች ልማት እንዲኖርና የከተማ ፕላን ለማስፋፋት እንዲሁም መስፈርት ላይ የተመሠረተ የከተሞች ፈርጅ የማደራጀት እና ከሚገኙበት የፈርጅ ደረጃ ወደሚቀጥለው እንዲሸጋገሩ የስልጠናና የቴክንክ ድጋፍ አገልግሎት እየሰጠ ይገኛል።
ኢንስቲትዩቱ ዋና ተግባሩ በመጀመሪያ የከተሞችን ፕላን ማዘጋጀት ነው። የፕላን ዝግጅቱ የገጠር ማዕከላት ጀምሮ እስከ ትላልቆቹ ከተሞች ድረስ ያሉ ከተሞች ፕላኖቻቸውን የማዘጋጃ ስራ ዋና ተግባር አድርጎ እየሰራ ነው። ፕላኖች ከተዘጋጁ በኀላ የአተገባበር ሂዳቱን ያለበት ደረጃ የመገምገም ተግባር በመፈፀም የከተሞች ክትመት እንዲኖር በክልሉ ውስጥ ያሉ ከተሞች አደረጃጀት ተሠርቷል። የፈርጅ ለውጥ ጥናት ተደርጎ በሚመለከታቸው አካላት የፈርጅ ለውጥ ጥናት ውሳኔ በማስወሰን አካቶ ሲሰራ ቆይቷል፡፡
መ/ኮ፦ አሁን በክልላችን ምን ያህል ከተሞች አሉ? ፕላን ያላቸውስ ምን ያህል ናቸው?
አቶ ፀጋዬ ኃይሌ፦ በክልላችን ከፈርጁ 5 እስከ 1 ድረስ ያሉ የከተሞች ብዛት 106 ናቸው። ከነዚህም ከ20 ሺህ በላይ ህዝብ ያላቸው ከተሞች 20 መሆናቸውንና በክልሉ ውስጥ ያሉ ሁሉም ከተሞች የየራሳቸውን በየደረጃው ያለው ፕላን አላቸው። ፈርጅ 4እና 5 ደረጃ ላለቸው ከተሞች መሠረታዊ ፕላን የተሰራላቸው ሲሆን ፈርጅ 3 እና ከዚያ በላይ ለሆኑ ከተሞች እስትራቴጂክ ፕላን ተዘጋጅቶላቸው በትግበራ ሂደት ላይ ይገኛል።

ከተሞች የደረጃ ለውጥ ከመደረጉ አስቀድሞ ፕላን ትግባራ እየተከናወነ መምጣቱ ሁሉም ከተሞች በየደረጃው የሚያስፈጋቸው ፕላን እንዲኖራቸው አድርጓል። አንዳንድ የፕላን ጊዜያቸውን የጨረሱ ከተሞችን በመለየት በፕላን ተካተው እንዲተገበሩ እየተሰራ ነው፡፡
መ/ኮ፦ የከተሞች አደረጃጀት እንዴት እየተሰራ ነው?


አቶ ፀጋዬ ኃይሌ፦ ለክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ምክር ቤት ለ7 ከተሞች ካሉባት ደረጃ ወደ ሚቀጥለው እንዲሸጋገሩ ኢንስቲትዩቱ ባቀረበው የከተሞች አደረጃጀት ጥናት መነሻን ተከትሎ ፈርጃቸው ተሻሽሏል፡፡ በዚህም መሠረት ከዳውሮ ዞን የዋካ እና ኢሳራ ባሌ ፈርጅ 3 ከተሞች ወደ ከተማ አስተዳደሪነት እንዲያድጉ ተደርጓል፡፡ ከቤንች ሸኮ ዞን የቢፍቱና የሸኮ ፈርጅ 3 ከተሞች በተመሳሳይ መልኩ ወደ ከተማ አስተዳደር ተሻግረዋል። በሌላ በኩልም ካሉበት ፈርጅ ደረጃ ማሻሻያ ያደረጉት የቦንጋ ከተማ አስተዳደር፣ የሚዛን አማንና የታርጫ ከተማ አስተዳደሮች ሲሆኑ የታርጫ ከተማ ከዚህ ቀደም ከነበረበት ፈርጅ 3 ወደ ፈርጅ2፣ የቦንጋ እና የሚዛን አማን ካሉበት ፈርጅ 2 ወደ ፈርጅ አንድ አድርገዋል።
መ/ኮ፦ በቅርቡ በአዲስ መልክ የተቋቋሙ የፈርጅ 3 ከተማ አስተዳደር መዋቅሮችን ወደ ስራ ከማስገባት አኳያ እየተሰራ ያለውን ተግባር እንዴት ይገለጻል?
አቶ ፀጋዬ ኃይሌ፦ በቅርቡ በአዲስ መልክ የተቋቋሙ የፈርጅ 3 ከተማ አስተዳደር መዋቅሮችን ማለትም የዋካ፣ ኢሳራ ባሌ፣ የቢፍቱ እና የሸኮ ፈርጅ 3 ከተሞችን ወደ ስራ ከማስገባት አኳያ ከክልሉ ፐብሊክ ሰርቪስ እና የሰው ሀብት ልማት ቢሮ ጋር በመቀናጀት መዋቅር ጥናት ተደርጎ በማጽደቅና አስፈላጊ ቅድመ ሆኔታዎችን በሟሟላት የራሳቸውን አደረጃጀት ወደ ስራ እንዲገቡ የማድረግ ስራ ተሰርቷል።


አዳዲሶቹ የከተማ አስተዳደሮች የህዝብን የልማትና መልካም አስተዳደር ጥያቄዎችን በቅርቡ መመለስ በሚችሉበት ሁኔታ የየራሳቸውን ሽግግር ምክር ቤት በማደራጀትና የራሳቸውን ዕቅድ በማጽደቅ በጅምር ስራ ላይ ናቸው፡፡ እነዚህ በአዲስ መልክ የተደራጁ 4ቱ የፈርጅ 3 ከተሞች በቅርቡ ቀጣይ ውጤታማ እንዲሆኑ የሚያስችል የተግባር ላይ ስልጠና ይሰጣል፡፡
መ/ኮ፦ የከተሞች ፕላን ምንድነው? ፕላን ዝግጅቱስ? እንዴት እየተተገበረ ይገኛል?
አቶ ፀጋዬ ኃይሌ፦ ፕላን ማለት በከተሞች ያለውን ውስን ሀብት ጠቃሜታ ባለው መንገድ ለኑሮ ምቹ እና ለስራ እንዲሁም ለማምረት አማች ህግ ነው። ከፕላን ዝግጅት አንፃር በክልሉ ከ20,000 በላይ ህዝቡ የሚኖርባቸው 20 ትላልቅ ከተሞች ስትራቴጂክ ፕላን ያላቸው ቢሆንም የቴፒ ከተማ በፕላን አተገባበር ላይ መሠረታዊ ችግር መኖሩን የፌዴራል ፕላን አተገባበር ቢሮ በሰጠው ግብረ መልስ መነሻ በማድረግ የቴፒ ከተማ ስትራቴጂክ ፕላን ዝግጅት ትግባራ ተጀምሯል። ስለሆነም ቴፒ ከተማ ከነበረው 2600 ወደ 6 ሺህ በላይ የማስፋትና የከተማዋን የአስተዳደር ወሰንና የመሬት አቅርቦት መመለስ የሚያስችል ለቀጣይ 10 ዓመታት ሊያገለግል የሚችል ስትራቴጂክ ፕላን እየተዘጋጀ ነው፡፡
በክልሉ ፕላን አዋጅ አንድ ከተማ እስትራቴጂክ ፕላን ከተዘጋጀላት በኀላ ሁለት የሠፈርልማት ፕላን መዘጋጀት አስጋዳጅ ሁኔታ መሆኑ በአዋጅ በግልፅ ተቀምጧል። ቦንጋ ከተማ የኮሪደር ልማት የተሰራውን አጠቃሎ ከተማዋን መልሶ መልማት እንዲያስችል 43 ሄክታር ላይ የሠፈር ልማት ፕላን ተዘጋጅተዋል የከተማው ዲዛይን ተሠርቷል፡፡
መ/ኮ፦ በፕላን ዙሪያ ለህብረተሰቡ ምን ማደረግ አለበት ይላሉ?
አቶ ፀጋዬ ኃይሌ፦ በክልሉ ለሚዘረጋው ለየትኛውም የከተማ ፕላን በየደረጃው ያለው አመራር እና ህዝብ አስተያየት እንዲሰጥበት እየተደረገ ነው፡፡ ህዝቡ መሠረታዊ የፕላን ይዘቶችን እንዲያውቅና የሚጠበቅባቸውን አስተዋጽኦ እንዲያበረክቱ ከማድረግ አንፃር እየተደረጉ ያሉ ጅምር ስራዎች መጠናከር መቻል አለባቸው።
መ/ኮ፦ ኢንስቲትዩቱ እየገጠመው ያለውን ማናቆች እየፈታ ከመሄድስ ይመለከቱታል?


አቶ ፀጋዬ ኃይሌ፦ ኢንስቲትዩቱ እየገጠመው ያለውን የሰው ሃይል፣ የበጀት እና የመሣሪያ እጥረት ችግሮችን እየፈታ ከመሄድ አንፃር በርካታ ጥረት እያደረገ ነው፡፡ ለዚህም የሰው ሀይልን ቀጥታ ስራ ልምድና ሙያ ብቃት ያላቸውን ከተለያዩ ቦታ በማሰባሰብ እየተጠቀመበት ቆይቷል፡፡ ለዘርፉ የሚያስፈልገው የመሣሪያና በጀት እጥረትን ለመፍታት የክልሉ መንግስት ጥረት እያደረገ ይገኛል፡፡ ለኢንስቲትዩት ተጠሪ የክልሉ ከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ቢሮ አውንታዊ ድጋፍ እያደረገ ነው፡፡ ስለሆነም በከተሞች አተገባበር ሂደት የሚስተዋሉ ችግሮችን ለመፍታት የተጀመሩት ጥረቶች ተጠናክረው ሊቀጥሉ ይገባል።
መ/ኮ፦ ለሰጡን ቃለ መረጃ እናመሰግናለን
አቶ ፀጋዬ ሀይሌ፦ እኔም እድሉን ስለሰጣችሁኝ አመሰግናለሁ!!
በተከተል ወ/ሚካኤል

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *