በሚዛን አማን ከተማ በአራት ቀበሌዎች 1 ሺህ 148 ይዞታዎች ወደ ህጋዊ ትግበራ መግባታቸው ተገለጸ ።

Spread the love

በሚዛን አማን ከተማ አስተዳደር እየተከናወኑ የሚገኙ የሴፍትኔት ፕሮግራሞች እና የማዘጋጃ ቤታዊ አገልግሎቶች ዙሪያ ምልከታ ተደርጓል ።

የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ቢሮ ኃላፊ ኢንጂነር የማታለም ቸኮል በከተማ አስተዳደር ተገኝተው ምልከታ አድርገዋል።

በምልከታው ወቅት የከተማው ማዘጋጃ ቤት ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ አሰፋ ቤሪ እንደገለጹት በክልሉ ደንብና መመሪያ ወጥቶ በስራ ላይ የሚገኘው ሳይፈቀዱ የተያዙ 2ሺህ 771 ይዞታዎችን ለይቶ በመመዝገብ 1 ሺህ 148 ይዞታዎች በአራቱምቀበሌ ወደ ትግበራ መግባታቸውን አስረድተዋል።

በክልሉ መስተዳደር ምክር ቤት ውሳኔ መሠረት ፈቃድ ከወሰዱ 18 ባለሃብቶች ውስጥ 9ኙ ሙሉ በሙሉ ወደ ተግባር የገቡ መሆናቸውንና ቀሪዎቹ ወደ ተግባር ለመግባት በሂደት ላይ መሆናቸውን አቶ አሰፋ አብራርተዋል።

የከተማ ልማታዊ ሴፍትኔት ፕሮጀክት ስራ ሂደት አስተባባሪ አቶ ታመነ ጨመዳ በበኩላቸው ከ2014 ዓ/ም ጀምሮ በህብረት ቀበሌ 403 የፕሮጀክት ተጠቃሚዎች ተመርቀው ለእያንዳንዳቸው ከ26 ሺህ ብር በላይ በመስጠት ወደ ቋሚ ስራ እንዲገቡ ተደርጓል ብለዋል።

የፕሮጀክቱ ተጠቃሚዎች በከተማ ግብርና በከብትና ዶሮ እርባታ፣በግ በማደለብ፣ በአገልግሎት ዘርፍ፣ በሴቶች የውበት ሳሎን እና በህፃናት አልባሳት ሽያጭ ተሰማርተው ተጠቃሚ እየሆኑ መሆናቸውን አስተባባሪው አስረድተዋል።

የክልሉ ከፍተኛ አመራሮች፣የቤንች ሸኮና የሚዛን አማን ከተማ አስተዳደር አመራሮች በከተማ አስተዳደሩ ማዘጋጃ ቤት በመገኘት የከተማ ልማታዊ ሴፍትኔት ስራዎችን፣ ሳይፈቀዱ የተያዙ ይዞታዎችን ፣ በከተማዋ የኢንቨስትመንት ፈቃድ ወስደው ወደ ስራ የገቡና በሂደት ላይ ያሉ አልሚ ባለሃብቶችናየመሰረተልማት ስራዎችን ተዘዋውረው ተመልክተዋል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *