




የአማራ ክልል ርእሰ መስተዳድር አረጋ ከበደ በባሕር ዳር ከተማ ከእርሳቸው ጋር ተገኝተው ሕዝባዊ ውይይቱን ለመሩት የሶማሌ ክልል ርእሰ መሥተዳድር ሙስጠፌ መሀመድ እና ለመንግሥት ተጠሪ ሚኒስትሩ ተሥፋዬ በልጂጌ የክብር ካባ አልብሰዋል።
ርእሰ መስተዳድር አረጋ “ወንድሜ ሙስጦፌ በሶማሌ ክልል የሚኖሩ ሁሉም ብሔር ብሔረሰቦች እኩል ተከብረው እና ደኅንነታቸው ተጠብቆ እንዲሠሩ እና እንዲኖሩ ያስቻሉ መሪ ናቸው” ሲሉ ተናግረዋል።
አማራ ክልል ችግር በገጠመው ጊዜ ሁሉ “የአንዳችን ችግር የሌላችንም ነው” በማለት ክልሉ ሰላም እንዲያገኝ በጋራ የሚሠሩ ሰው ስለመኾናቸውም ርእሰ መስተዳድር አረጋ ገልጸዋል።
ዛሬም “ሰላም የለውም እየተባለ የሐሰት ፕሮፖጋንዳ ወደሚነዛበት ክልል በመዝለቅ የሕዝቡን ጥያቄ በመስማታቸው እናመሠግናቸዋለን” ብለዋል። የክብር ካባውንም በሕዝብ ወኪሎች ፊት አልብሰዋቸዋል።
ሌላው የክብር ካባ የለበሱት የመንግሥት ተጠሪ ሚኒስትር ተስፋዬ በልጅጌ ናቸው።
ሚኒስትሩ የአማራ ክልል ሕዝብ ችግር የሁላችንም ችግር ነው በማለት ወደ ባሕር ዳር ዘልቀው በሕዝብ ፊት በመቆም ጥያቄዎችን ተቀብለዋል።
ጥያቄዎች በውይይት ተፈትተው የክልሉ ሕዝብ ሰላም እንዲመለስ እንደሚሠሩም ገልጸዋል።
በዚህ ወቅት የክልሉ ሕዝብ የገጠመውን ችግር በመረዳት ወደቦታው መጥተው ለዘላቂ መፍትሔው በጋር የሚሠሩ ስለመኾኑ ነው የክብር ካባው የተበረከተላቸው።
እንደ አሚኮ ዘገባ፤ ሁለቱም መሪዎች በአማራ ክልል ሕዝብ ስም ለተሰጣቸው ክብር አመስግነዋል።
ሕዝቡ በአጭር ጊዜ ውስጥ ሰላሙን አግኝቶ በሙሉ አቅሙ ወደ ልማት እንዲገባ በአንድነት እንደሚቆሙም አረጋግጠዋል ሲል ደሬቴድ ዘግቧል።
