ተቋርጦ የነበረውን የቴፒ አይሮፕላን ማረፊያ መልሶ ወደ ስራ ለማስገባት በሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ ከማሻ ከተማ ነጋዴዎችና የግል ባለሀብቶች ጋር የውይይት መድረክ ተካሄደ።

Spread the love

የማሻ ወረዳና የከተማ ነዋሪዎች በበኩላቸው ለእቅዱ እውን መሆን የበኩላቸውን እንደሚወጡ ተናግረዋል።

በመድረኩ ላይ የተገኙት የሸካ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ አበበ ማሞ ዞኑ እምቅ የተፈጥሮ ሀብት ባለቤት ብቻ ሳይሆን ሰፊ የመልማት እድል ያለው ከመሆኑ ጋር ተያይዞ መሰል የትራንስፖርት አገልግሎት ማስፈለጉን ተናግረዋል።

ከዚህ ቀደም ምንም ስልጣኔ ባልተስፋፋበት ወቅት የቴፒ አየር ማረፊያ ከ1950 ዓመተ ምህረት ጀምሮ አገልግሎት እየሰጠ ነበረ ያሉት አቶ አበበ በተለያዩ ምክንያቶች ተቋርጠ እንደነበረ ተናግረዋል።

የአውሮፕላን ንግድ ፍቃድ ያላቸው የግል ባለሀብቶች ለዞን ህዝብ ምቹ የትራንስፖርት አገልግሎት ለመስጠት ጥያቄ እያቀረቡ ይገኛሉ ያሉት አቶ አበበ በዚህ ተጠቃሚ ለመሆን አየር ሜዳውን በማጠር ምቹ የማረፊያ ቦታ ለማድረግ ሊሠራ እንደሚገባ ጠቁመዋል ።

ይህን በተመለከተ በቴፒ ከተማ ከሁሉም ማህበራዊ መሰረት ከተገኙት አካላት ጋር ውይይት የተደረገ ሲሆን 7 ኮሚቴ በማዋቀር የተለያዩ ስራዎች መጀመራቸውንም ጠቁመዋል።

በማሻ ከተማና ወረዳ ኮሚቴ ተዋቅሮ ሀብት የማሰባሰብ ስራ እንደሚሰራም ተናግረው ይህም ተግባራዊ ሲሆን የዞኑ ህዝብ በፈለገበት ቦታ ያለምንም መጉላላት መድረስ የሚችል መሆኑ ብቻ ሳይሆን ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ እንዳለው ጠቁመዋል።

ይህም ለዞኑ ቱሪዝምና ኢንቨስትመንት ማደግ ምቹ ሁኔታ እንደሚፈጥር ተናግረዋል።

አገልግሎቱ ሳይቋረጥ በፊት የቴፒ አየር ማረፊያ ከ70 አመት በፊት አገልግሎት እየሰጠ የቆየ መሆኑን የገለፁት ኮሚቴዎች በወቅቱ በቀን 3 አውሮፕላኖች አገልግሎት እየሰጡ እንደነበረ ጠቁመዋል።

በውይይት መድረኩ ላይ በማሻ ወረዳ በኢንቨስትመንት ዘርፍ የተሰማሩ አካላት ተወካችና በማሻ ከተማ የሚገኙ የነጋዴ ማህበረሰብ ክፍሎች የተገኙ ሲሆን በዞኑ

የንግድ ትስስር ለማጠናከር ፣ኢንቨስትመንት ለማስፋፋት ፣በቱሪዝም ዘርፍ ውጤታማ ለውጥ ለማስመዝገብ እንዲሁም ያለውን የተፈጥሮ ሀብት ማሳወቅ ላይ ትኩረት መስጠት አስፈላጊ መሆኑ ተመላክቷል።

ለአየር ማረፊያ ምቹ ሁኔታ ከተፈጠረ በሳምንት ለ55 ሰዎች አገልግሎት መስጠት እንደሚችል የተገለፀ ሲሆን ይህም አሃዝ የተጠቃሚዎች ቁጥር ከጨመረ እያደገ የሚሄድ እንደሆነ ተገልጿል ።

የውይይቱ ተሳታፊዎች በበኩላቸው የሸካ ዞን በተለይም ቴፒ ከተማ ብዙ የመልማት አቅም ያላት ከተማ እንደመሆኗ የቴፒ አየር ማረፊያን ወደ ስራ ለማስገባት በሚደረገው እንቅስቃሴ ላይ አስፈላጊውን በማድረግ የበኩላቸውን እንደሚወጡ ጠቁመዋል ሲል ደሬቴድ የማሻ ቅርንጫፍ ዘግቧል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *