




የሸካ ዞን ምክርቤት የዘርፍ ቋሚ ኮሚቴ በስሩ የሚከታተላቸዉን የአስፈጻሚ አካላት የ2016 በጀት ዓመት የ6 ወራት የአፈፃፀም ሪፖርት በሸካ ዞን ማሻ ከተማ ገምግሟል ።
መድረኩን የመሩት የሸካ ዞን ዋና አስተዳዳዳሪ አቶ አበበ ማሞ በወቅቱ እንደገለጹት በግማሽ ዓመቱ የታዩትን ጠንካራ ጎኖች በማስቀጠልና ድክመቶችን በማረም በህብረሰቡ ተጠቃሚነት ላይ በትኩረት መስራት ያስፈልጋል ብለዋል።
ዋና አስተዳዳሪው ከግብዓት ገንዘብ አሰባሰብ ጋር ያሉትን ውስንነቶች ተደጋግፎ መስራት እንደሚጠበቅና ከግብርና ልማት ስራዎችም አንጻር መሻሻሎች ቢኖሩም ከገበያ ትስስር ጋር ተያይዞ በቀጣይ ልዩ ትኩረት የሚሹ ጉዳዮች ናቸው ብለዋል።
በተለይም ከቴክኖሎጂ አጠቃቀም ባህል ጋር አምጻራዊ ለውጦች ቢኖሩም ትኩረት የሚሹ ጉዳዮች እንዳሉም አብራርተዋል።
በምክር ቤቱ የማህበራዊ ዘርፍ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ፣ የኢኮኖሚ ዘርፍ ጉዳዮች እንዲሁም የህግ ፍትህና መልካም አስተዳደር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ዝርዝር የስድስት ወራት አፈጻጸም ሪፖርት ቀርቦ ውይይቶችና ምክክሮች ተደርጎባቸዋል።
በግብርና ዘርፍ እርሻን በኩታ ገጠም የማምረት ሂደት እየተሻሻለ መምጣቱ ፣ የአርሶአደሩ ግንዛቤ ከወትሮው እያደገና እየተሻሻለ መምጣቱ የተሻለ አፈፃፀም መመዝገብ መቻሉንና በሌላም በኩል ከግብዓት አቅርቦት ጋር ተያይዞ የነበሩት ውስንነቶች ተፈተው ለአርሶ አደሩ ተጠቃሚነት ላይ እንዲሰራም ተገልጿል ።
ከእንስሳት እና ዓሳ ሀብት ልማት ስራዎች አንጻር የዓሳ ጫጬት ወደ ኩሬ የማስገባቱ ሰራ በዞኑ ውስጥ ባሉት ውስን ቦታዎች የተጀመረ መሆኑ በቀጣይ በሁሉም አካባቢዎች ትኩረት ተሰጥቶት መሰራት እንዳለበት ተጠቁሟል ።
የሸካ ዞን ዋና አፈጉባኤ አቶ ዮሀንስ ካሳሁን በበጀት ዓመቱ በጥንካሬ ከተገመገሙት ይልቅ ክፍተቶችን በመልቀምና በማረም በቀጣይ ቀሪ ጊዜያት መስራት እንደሚያስፈልግና በዋናነት ከትምህርት ስራዎች ጋር ተያይዞ የነበረውን የውጤት ማሽቆልቆል ፈር ለማስያዝ መትጋት ይጠበቃል ብለዋል።
በቀበሌያት በህብረተሰብ ተሳትፎ እየተገነቡ የሚገኙ የመንገድ ግንባታዎች በበጀት ዓመቱ የተሻሉ አፈፃፀም ያሳዩ በመሆናቸው ቀጣይ በሌሎችም ዘርፎች ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ተመላክቷል።
በአፈጻጸም ግምገማው መነሻም አፈጻጸሞች በጉድለትና በጥንካሬ የተገመገመበትና በዋናነትም እንደጉድለት ከተነሱት መካከል አልሚ የግል ባለሀብቶች ለገቡት የሰራ ዓለማ ህብረተሰቡን ተጠቃሚ የማድረግ ህደቶች ላይ ትኩረት ያለማድረግ ውስንነቶች መኖር፣ በመንግስት በኩል የተያዙ ካፒታል ፕሮጀክቶች ፈጥነው ወደ ስራ ያለመግባት፤ የጥምር ፍትህ ኮሚቴ አባላት ተግባራትን በቅንጅት ከመምራት አንፃር ክፍተቶች መኖርና አፈፃፀሙ ዝቅተኛ መሆን፤በከተሞች የቤት ልማት አማራጮች የሚውል መሬት ለአልሚዎች ከማድስ አንፃር ቀጣይ ትኩረት መሰጠት እንደሚያስፈልግ የሚሉትና ለሎች ሀሳቦች ተነስተዋል።
በሌላም በኩል የመንግስትና የህዝብ ሀብቶችን ኦድት ከማድረግና ከማስመለስ የነበሩትን የክትትልና ቁጥጥር አግባቦች በትኩረት እንዲሰራና በትምህርት ስራ ዘርፎች ለተማሪው ውጤት መሻሻል መላውን የትምህርት ባለድርሻ አካላቶችን በማሳተፍና በማስተባበር መስራት እንደሚያስፈልግና በሌላም በኩል ከቅጥርና ምደባ ስርዓት ጋር ያለውን ማነቆ በመፍታት ለአፈጻጸም መሻሻል እንድሰራ ተጠይቋል።
የግምገማው መድረክ በበጀት ዓመቱ ስድስት ወራት በቋሚ ኮሚቴው የሚከታተሏቸዉን አስፈጸሚ ተቋማት በዋና ዋና ተግባራት ላይ ያስመዘገቡ አመርቂ ውጤቶችን ማስቀጠልና መሻሻል ባለባቸው ጉዳዮች ላይ ተጠናክሮ መስራት እንዳለባቸው ተጠቁሟል።
በመድረኩ የዘርፉ ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢዎችና አባላት ፣ የአስፈፃሚ ተቋማት የስራ ኃላፊዎችን ጨምሮ ለሎች የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል ሲል የዘገበው የሸካ ዞን መንግሥት ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት ነው።
